Fana: At a Speed of Life!

ህፃናትና የትምህርት ተቋማት ህዝቡ ከነበረበት የድህነትና ኋላ ቀርነት አዙሪት እንዳይወጣ የሚፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ተቋማት የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪ አቀረበ፡፡
የክልሉ መንግስት ባስተላለፈው ጥሪ የትምህርት ተቋማት ህዝቡ ትናንት ከነበረበት የድህነትና ኋላ ቀርነት አዙሪት እንዳይወጣ የሚፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሊሰራ ይገባል ብሏል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዛሬ በመግለጫው እንዳታወቀው መንግስት የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄ በተሟላ መልኩ ለመመለስ እየሰራ ይገኛል፡፡
የክልሉ ህዝብ የረዥም ዘመናት የልማት፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሰራሁ ነውም ነው ያለው፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል::
በገጠር እና ግብርና ልማት የከተማ እና የገጠሩን ነዋሪ ባሳተፈ መልኩ በመስራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ረዥም ርቀት መሄድ ተችሏል ነው ያለው፡፡
በዚህም ከዚህ በፊት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሲገዛ የነበረውን ምርት መተካት እየተቻለ መሆኑን ገልጿል፡፡
ባለፈው አመት በተሰራው ስራ ከውጭ ሀገር ሲገባ የነበረን የቢራ ገብስ በሀገር ውስጥ መተካት እየተቻለ መሆኑን አብራርቷል፡፡
በዚህ አመት ደግሞ በክላስተር በማምረት የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በአስተማማኝ ደረጃ ማድረስ መቻሉን ነው ቢሮው የገለፀው፡፡
በበጋ ወራት በመስኖ እና በውሀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስንዴን በማልማት ከውጭ ሀገር ይገባ የነበረን ምርት ለመተካት የተወሰደው እርምጃ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው ሲል አብራርቷል፡፡
የኢኮኖሚ ልማትን ለማሻሻል እና የገበያ ትስስርን ለማሳለጥ ለመሰረተ ልማት ስራዎች በክልልና በሀገር ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ለማህበራዊ ልማት በተሰጠው ትኩረት የትምህርት ቤቶች ግንባታ እና ማስፋፊያ፣ የጤና ተቋማት እና ማህበራዊ ግልጋሎት የሚሰጡ ሌሎች ተቋማት ስራ በስፋ እና በጥራት እየተሰራ ይገኛል ነው ያለው፡፡
በሰባት ወራት ውስጥ ብቻ 147 ልዩ አዳሪ፣ ልዩ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፤ አፈፃፀማቸውም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ሲል ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ህዝባችን ትናንት ከነበረበት የድህነትና ኋላ ቀርነት አዙሪት እንዳይወጣ የሚፈልጉ ኃይሎች ህፃናትን መጠቀሚያ በማድረግ በተወሰኑ አካባዎች ብጥብጥ ለማስነሳት ሞክረዋል ብሏል ቢሮው፡፡
መንግስት የህዝቡን እና የትምህርት ተቋማትን ደህንነት ለማስጠበቅ ባለበት ግዴታ መሰረት ስራውን የሚወጣ ይሆናል ብሏል፡፡
ህፃናትን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚውተረተሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ቢሮው አሳስቧል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ የትምህርት ተቋማት የአፍራሽ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ቤተሰብ እና ህብረተሰቡ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላፏል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.