Fana: At a Speed of Life!

በከተሞች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የቅንጅት ስራ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከተሞች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የቅንጅት ስራ አስፈላጊ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህንፃ ኮሌጅ አመራሮች ጋር በከተሞች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ምክክር አድርጓል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ቤቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ መስፍን አሰፋ፥ በከተሞች ከቤት አቅርቦት፣ ከመሬት አስተዳደር፣ ከከተማ ፕላን፣ ከከተማ ፅዳትና አረንጓዴ ልማት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

አያይዘውም ከአቅም ግንባታ እና በዘርፉ የሚታየውን የሃብት ብክነት ለማዳን ስራዎችን በጋራ ተናቦ በቅንጅት መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው በትልልቅ ከተሞች የሚታዩት የተቀናጀ መሰረተ ልማት ችግሮች በአዳዲስ ከተሞች እንዳይደገሙ ችግር ፈች ጥናቶችን ከማድረግ ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ስራዎችን በዕቅድ ለመምራት እንዲቻልም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጣ ኮሚቴ መዋቀሩን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.