Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይቱ ወቅት አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የመልሶ ማቋቋምና የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታን በተመለከተ ለልዩ መልዕክተኛው ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

መንግስት አሁን ላይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍና የወደሙ መሰረት ልማቶችን የመገንባት ስራ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ ጋር በተያያዘም 26 ድርጅቶች ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስ ስራ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል አቶ ደመቀ፡፡

አቶ ደመቀ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን አጋርነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ክልል ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያወጣውን መግለጫ በተመለከተም የመንግስትን አቋም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ህብረቱ ሁኔታውን እንዲረዳና ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች እንድትወጣ እንደ ስትራቴጂክ አጋርነቱ ገንቢ ሚና እንዲጫወትም ጠይቀዋል፡፡

ከሱዳን ጋር ስላለው የድንበር ውዝግብ በሰጡት ማብራሪያም ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን አቋም አንስተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ስለሽ በቀለ፥ እየተካሄደ ያለውን ድርድር ለመቋጨት ያላትን ዝግጁነት በተመለከተ ለልዩ መልዕክተኛው ገልጸውላቸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሌሎች ሃገራትም በአፍሪካ ህብረት በተቀመጠውና ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው ማዕቀፍ መሰረት ይህንኑ የኢትዮጵያ መንገድ እንዲከተሉ አሳስበዋል፡፡

የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ሃቪስቶ ፔካ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል በተለያዩ የትብብር ዘርፎች ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት መንግስት በትግራይ ክልል ላለው ሰብአዊ ሁኔታ እየሰጠ ያለውን ምላሽ ይረዳል ያሉት ልዩ መልዕክተኛው በክልሉ እየተደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.