Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ ምክር ቤት የትራምፕን በኢራን ላይ ጦር የማዝመት ስልጣን ገደበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን በኢራን ላይ ጦር የማዝመት ስልጣን የሚገድብ ውሳኔ አሳለፈ።

ውሳኔው ዴሞክራቶች በተቆጣጠሩት ምክር ቤት 224 ለ194 በሆነ ድምጽ አልፏል።

ይህም ትራምፕ ሃገራቸው ከቴህራን ጋር የገባችውን ፍጥጫ ተከትሎ በኢራን ላይ ጦር ማዝመት እንዳይችሉ የሚያደርግ ታሪካዊ ውሳኔ ነው ተብሏል።

የአሁኑ ውሳኔ ዋሽንግተን ከኢራን ጋር አስገዳጅ ግጭት ውስጥ ካልገባች በቀር ጦሯን ቴህራን ላይ የማዝመቱን ውሳኔ ለኮንግረሱ የሚሰጥ ነው።

ይህም ትራምፕ ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ቢፈልጉ የኮንግረሱን ይሁንታ እንዲያገኙ የሚያስገድድ ነው።

ከዚህ ባለፈም ትራምፕ ውሳኔውን ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው መሻር አይችሉም።

ኮንግረሱ ፕሬዚዳንቱ ኢራን ላይ ጦር ማዝመት ቢፈልጉ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ እርምጃውን ማስቆም መቻል አለመቻሉ ግን አሁንም ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ጀኔራል ቃሲም ሱለይማኒን ከገደለች በኋላ ሁለቱ ሃገራት ከባድ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።

ሃገራቱ ወደለየለት ግጭት ይገባሉ ተብሎ ቢሰጋም እስካሁን ከቃላት ጦርነት ያለፈ ወደ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አልገቡም።

የምክር ቤቱን ይሁንታ ያገኘው ውሳኔ ለመጽደቅ በሴኔቱ ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.