Fana: At a Speed of Life!

በዓመት ከ3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይሰጣል የተባለው የበለስ ስኳር ፋብሪካን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓመት ከ3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይሰጣል የተባለው የበለስ ስኳር ፋብሪካን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

ይህንን ያስታወቁት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወዮ ሮባ ናቸው፡፡

የስኳር ፋብሪካው ከሰባት ዓመታት በፊት ከ235 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ፈሶበት ወደ ስራ ቢገባም በታሰበው ልክ ወደ ምርት መግባት እንዳልቻለ ተመላክቷል።

ግንባታውን ያካሄደው የቀድሞው ብርታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ስራውን ከማጓተት ባለፈ የተሰሩት ስራዎች ከደረጃ በታች የሆኑና ስኳር ማምረት የማያስችሉ ሆነው መገኘታቸውን አቶ ወዮ አስታውሰዋል።

ችግሩን በጥልቀት በመገምገም ፋብሪካው ካለበት ውስብስብ ችግር እንዲወጣ ከአንድ ዓመት በፊት ለአዲስ የቻይና ተቋራጭ ስራው እንደተሰጠ ገልጸዋል።

በወቅቱ ፋብሪካው 65 በመቶ ግንባታው ተሰርቷል ተብሎ ስለነበር 35 በመቶ የሚሆነውን አዲስ ውል ተገብቶ ወደ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።

“ይሁንና በግንባታው ላይ ከፍተኛ የሆነ የጥራት ችግር በማጋጠሙ ተሰሩ የተባሉ ስራዎች ጭምር እየፈረሱ እንደ አዲስ ተሰርተዋል” ብለዋል።

ለግንባታው ከፍተኛ ሃብትና ንብረት ከመፍሰሱ ባለፈ ፋብሪካው ፈጥኖ ወደ ማምረት ባለመግባቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።

በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ግንባታውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደ ምርት ለመግባት ታስቦ ወደ ስራ ቢገባም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክስተት በተባለው ጊዜ ማድረስ እንዳልተቻለ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የሰው ሃይል በመጨመርና ትርፍ ሰዓት በመስራት ግንባታውን 87 ነጥብ 7 በመቶ ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገለጻ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፋብሪካውን ወደ ምርት ለማስገባት እየተሰራ ነው።

ፋብሪካው ፈጥኖ ወደ ማመረት ባለመግባቱ በ13 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ከነበረው የሸንኮራ አገዳ ውስጥ 11 ሺህ ሄክታሩ ለብልሽት መዳረጉን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው በቀን 120 ሺህ ኩንታል አገዳ በመፍጨት 12 ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም እንዳለው አመልክተዋል።

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በዓመት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰጣል።

ይህ ደግሞ አገሪቱ በዓመት ከውጭ የምታስገባውን 2 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል።

ፋብሪካው ስኳር ከማምረት ባለፈ የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነሳሳት ለተሻለ የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመላክተዋል።

“ስኳር ፋብሪካው ተገንብቶ ወደ ማምረት እንዲገባ የክልሉ መንግስት ማገዝ ያለበትን ያግዛል” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው።

ፋብሪካው በአገሪቱ የሚስተዋለውን የስኳር አቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ለስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እንዳለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-

https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.