Fana: At a Speed of Life!

በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ“ያገባኛል ”ኢንሼቲቭ  ትግበራ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ“ያገባኛል ”ኢንሼቲቭ  ትግበራ በይፋ ተጀምሯል።

በጤናው ዘርፍ የመጀመሪያው አገር በቀል ኢንሼቲቭ የሆነውና የጤናውን ስርዓትና አገልግሎት ይለውጣል ተብሎ የተቀረፀው “ያገባኛል ” የተሰኘው ኢንሼቲቭ  እንደ ሀገር በ24 ሆስፒታሎች ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ስራ መገባቱ ተገልጿል።

በአማራ ክልል ኢንሼቲቩ ተግባራዊ እንዲደረግባቸው ከተመረጡት አራት ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የሆነው የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጥናትን መሰረት ያደረገ የእቅድ ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ተግባር መግባቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በአጭር ጊዜ ትልቅ ውጤት ላይ መድረስ የኢንሼቲቩ ጥቅል ግብ ሲሆን የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት፣ የአሰራር ማሻሻያ፣ ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር እና ሌሎች ጉዳዮች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

ትግበራው መጀመሩን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው መድረክ ላይ  ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ÷ ለህብረተሰቡ ጥቅም ተብለው የሚቀረፁ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ሆነው ተገልጋዩን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ሁላችንም የሚጠበቅብንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡

አያይዘውም እንደተናገሩት ኮቪድ-19ን ፊት ለፊት እየተጋፈጡ ያሉት የጤና ባለሙያዎች ተገቢው ክብር ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው÷ ከችግሮች መላቀቅ የሚቻለው የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ችግሮችን ወደ ሌላ አካል መግፋትን በመተው የመፍትሄ አካል መሆን ሲቻል  ነው ብለዋል።

በክልሉ ኢንሼቲቩ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው ሆስፒታሎች ልምድ ተወስዶ በሂደት ወደ ሌሎች እንደሚስፋፋም አሳውቀዋል፡፡

በዋናነት ለውጥ የሚገኘው በውስጥ አቅም መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሰይድ ዩሱፍ ሲሆኑ ÷ሁሉም በባለቤትነት ስሜትና የተግባር አካል መሆን እንዳለበት በማሳሰብ ኢንሼቲቩ በሆስፒታሉ ተግባራዊ እንዲሆን የከተማው አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ያዕቆብ ሰማን ኢንሼቲቩ ተግባራዊ የሚደረግባቸው ሆስፒታሎች ውስን የሆኑት በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሆስፒታሎች በአንድ ጊዜ ማስጀመር ስለማይቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ያዕቆብ አያይዘውም የጤና ሚኒስቴር ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው÷ በክልሉ አመራሮች፣ በተቋሙ ባለሙያዎች እና በህብረተሰቡ ዘንድ የተስተዋለው ተነሳሽነት የኢንሼቲቩ እቅድ ወደ ተግባር ተቀይሮ ስኬታማ እንደሚሆን አያጠራጥርም ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.