Fana: At a Speed of Life!

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሶስት ግለሰቦች እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሶስት ግለሰቦች እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የሽረ እንዳስላሴ ከተማ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳለፈ።

በትግራይ ክልል የሽረ እንዳስላሴ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ገብረሚካኤል ገብረስላሴ እንደገለጹት ፥ ግለሰቦቹ ቅጣቱ የተወሰነባቸው 25 ሽጉጦች በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ በመገኘታቸው ነው።

ግለሰቦቹ  መሳሪያዎቹን ይዘው ሲያዘዋወሩ በህዝብ ጥቆማና በፀጥታ ሃይሎች ክትትል ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በከተማዋ እጅ ከፈንጅ መያዛቸውን የገለጹት አዛዡ፤ ፖሊስ  ምርመራውን በፍጥነት አካሂዶ ለከተማዋ ፍርድ ቤት በማቅረቡ ውሳኔው እንደተላለፈባቸው አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ የቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው ቅጣቱን እንደወሰነባቸው ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት አንደኛው ተከሳሽ ሻተይ አዳነ ሲሳይና ተባባሪው ኢሳያስ ዓርዓዶም ፀጋይ እያንዳንዳቸው  በ5 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ፈርዶባቸዋል።

እንዲሁም ግለሰቦቹን በተሽከርካሪ ሲያንቀሳቅስ የነበረው ሓበን አልጋው ብርያኑ በ4 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.