Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ጋር ተወያዩ 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ሳሚ ጀሚል አብዱላህ ጋር ተወያዩ፡፡

አቶ ደመቀ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት በማውሳት፣  ግንኙነትን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደው የህግ ማስከበር እርምጃ መጠናቀቁን ተከትሎ  የረድኤት ድርጅቶችና የሚዲያ አካላት በክልሉ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ስለመፈጠሩ፣ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ስለመገንባት፣ ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት ገለልተኛ ተቋማት ከአፍሪካ ህብረትም ሆነ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ተባብሮ ለመሥራት  የመንግስት  ዝግጁነትን አስታውሰዋቸዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተም ኢትዮጵያ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ አስተባበሪነት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ፍላጎቷ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሱዳን እና በግብፅ በኩል እየቀረበ ያለው አዲስ የድርድር ሃሳብ ለኢትዮጵያ ወገን ይፋዊ በሆነ መልኩ ያልቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ በአገራቱ መካከል የሚፈጠሩ ልዩነቶች በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት መፍታት የሚቻል መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት፡፡

የኢትዮ-ሱዳን  የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘም፤ ሱዳን የያዘችውን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ስትለቅ በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ሚኒስትሩ በሳዑዲ ዓረቢያ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን አንስተው፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ሳሚ ጀሚል አብዱላህ በበኩላቸው በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ላይ ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፣ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵውያን ወደ አገራቸው አንዲመለሱ በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ድጋፉን እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ  ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.