Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ የህዝብና የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ ሊደረግ  ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ ማናቸውም የህዝብና የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከሚያዝያ 1 ቀን ጀምሮ  የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ ሊደረግ  ነው።

በዚህም በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አገጣጠምና ጠቀሜታው ላይ ያተኮረ ስልጠና ለህዝብ እና ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች እንዲሁም ለትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችና የትራፊክ አባላት መስጠቱ ተገልጿል።

በስልጠናው ላይም በተያዘው  ወር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ በርካቶች ለህልፈት እንዲሁም ለአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ሰለባ በመሆን ላይ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው፡፡

ለእነዚህ አደጋዎች  በመንስኤነት ከተለዩት መካከል አንዱና ዋነኛው ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር መሆኑን የገለፁት በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰአዳ አዋሌ ናቸው፡፡

በመሆኑም በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ  ዜጎችን  ህይወት ለመታደግ  የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያን  ወደ ትግበራ ለማስገባት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል።

ሃላፊዋ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ከሚደረገው የማስተማርና ማስገንዘብ ስራ በተጓዳኝ መሰል ህጎች እንዲከበሩ ተሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን ጠብቀው እንዲያሽከረክሩ የቁጥጥር ስርአቱ ይጠናከራል ብለዋል።

ለዚህም ከሚያዚያ አንድ ጀምሮ ማንኛውም ተሽከርካሪ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያን እንዲያስር ህጉን በማስከበር ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ይሰራል ማለታቸውን ከድሬዳዋ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.