Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሁሉንም አካታችና ተደራሽ እንዲሆን ሀገራት አበክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሁሉንም አካታችና ተደራሽ እንዲሆን ሀገራት አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ፕሬዚዳንቷ ይህንን ያሉት “የዲጂታል አካታችነት” ላይ ያተኮረው ውይይት በበይነ መረብ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

የዓለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ልማት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት አጋዥ የሆነው “ወደ አዲስ ጉዞ” የተሰኘው ተከታታይ ዝግጅት አካል “የዲጂታል አካታችነት” ላይ ያተኮረ ውይይት በበይነ መረብ ተካሂዷል።

መድረኩን የከፈቱት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካታች ማድረግ ላይ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ፈተናዎች የተደቀኑበት ነው ብለዋል።

የዓለማችን ክፍል ግማሹ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንኙነት ውጪ መሆኑ ያሳዝናል ያሉት ፕሬዚዳንቷ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሁሉንም አካታችና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ሀገራት አበክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የዲጂታል አካታችነትን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋገጡት ፕሬዚዳንቷ ይህንን እውን ለማድረግ የብሄራዊ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ተቆጣጣሪና የኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን መቋቋሙን አንስተዋል።

የዝግጅቱ ዋና ትኩረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አካታችነት ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችንና አቅም የሌላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በዘርፉ እኩል ተጠቃሚ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ልማት ኮንፈረንስ በቀጣይ ዓመት በኢትዮጵያ የሚደረግ ሲሆን የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.