Fana: At a Speed of Life!

የጤና ሚኒስቴር 8ኛው ዙር የሀገሪቱን የጤና ወጪ ጥናት ማስጀመሪያ ለህዝብ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት 8ኛው ዙር የሀገሪቱን የጤና ወጪ ጥናት ማስጀመሪያ ለህዝብ ይፋ አደረገ፡፡

ጥናቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ ከአጋር ድርጅቶች፣ ከመንግስት እና ከግል ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የጤና ወጪ ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና ለጤናው ዘርፍ የሚውለውን የሀብት ፍሰት ለመከታተል በርካታ ሃገሮች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ዘዴው ለዘርፉ የሚወጣውን አጠቃላይ ሀብት ከመነሻው ማለትም ሀብቱን ከሰጠው/ካመነጨው አካል እስከመጨረሻው ማለትም ሀብቱ ለምን ጥቅም እንደዋለ በዝርዝር ይመረምራል፡፡

በተጨማሪም የወጣው ወጪ በማን ወይም በየትኛው አካል እንደሚተዳደርና ለተጠቃሚው የሚቀርቡ የጤና አገልግሎቶችም በየትኛዎቹ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንደተሰጡ በዝርዝር ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ተደራሽነትና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመላው ህብረተሰብ ለማዳረስ በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት፣የጤና ወጪ የጥናት ግኝቶችን በየጊዜው ለሚወስዳቸው የፖሊሲ ውሳኔዎችና የሀብት አመዳደብ ሥርዓት በግብዓትነት ሲጠቀምባቸው መቆየቱና አሁንም በመጠቀም ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ለስምንተኛ ጊዜ የሚካሄደው የአሁኑ ዙር የጥናት ወጪ የሚሸፈነው በመንግስት እና በዘርፉ የልማት አጋሮች እንደሚሆንም ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.