Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ከሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ጋር ለሚተባበሩ አካላት የመጨረሻ ማሳሰቢያ ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ከሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ጋር ለሚተባበሩ አካላት የመጨረሻ ማሳሰቢያ ሰጠ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫውም መንግሥቱን እና ሌሎች የሀገሪቱን መሠረታዊ ሕጎች በመጣስ በሕወሓት ውስጥ የበላይነቱን የያዘው ቡድን፣ የሀገር አለኝታ እና ኩራት በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የኃይል ጥቃት መሰንዘሩን አስታውሷል።

ከዚህ ጥቃትም አስቀድሞ፣ የጥቃቱ ጠንሳሽ የሆነው ቡድን፣ የሀገርን ሰላም እና የሕዝቦችን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የተለያዩ ሕገ ወጥ ተግባራትን ሲፈጽም ነበር ብሏል ፅህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ፡፡

ይህ ሕገ ወጥ የሕወሓት ቡድን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በፈጸማቸው የጥፋት ተግባራት የሰላም መደፍረስ፣ የዜጎች ሞት እና መፈናቀል እንዲሁም አካባቢያዊ መናጋት ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ችግሩን በሰላማዊ መንግድ ለመፍታት ያሳየውን ትዕግሥት እንደ ድክመት በመቁጠር ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ሀገርን የመድፈር ወንጀል ፈጽሟልም ብሏል፡፡

በተለይም በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ሰፊ ጥቃት ሊታለፍ የማይችል እና የሀገርን ህልውና የሚፈታተን ትልቅ ወንጀል መሆኑን ያነሳው መግለጫው፥ ይህ ሁኔታ መንግሥት ተገቢ ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲወስድ የሚያስገድድ ቅርብና ግልጽ አደጋ የደቀነ እንደነበርም አውስቷል፡፡

እንዲህ ያለ ነገር ሲፈጠር መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ተገቢውን ሕግ የማስከበር እርምጃ የመውሰድ የሞራል እና የሕግ ግዴታ እንዳለበት እሙን ነውም ብሏል መግለጫው።

ይህን ግዴታውን ለመወጣት የፌደራል መንግሥት በሕወሓት ሕገ ወጥ ቡድን ላይ የሀገሪቱ ሕግ የሚያዘውን እርምጃ መውሰዱንም አስታውሷል፡፡

በዚህ እርምጃም ከሀገር አልፎ ለቀጠናው ሥጋት ሆኖ የቆየው የሕወሓት ሕገ ወጦች ቡድን ከፍተኛ ወታደራዊ አቅም እና ዝግጁነት መደምሰሱንም ጠቅሷል።

የዚህ ቡድን ቁልፍ አመራር የሆኑት ግለሰቦች ከፊሎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ለሕግ የቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ አቅማቸው እና ኃይላቸው እጅጉን ተዳክሞ፣ ከሕግ በመሸሽ የሚባዝኑ የፍትሕ ተሳዳጆች መሆናቸውንም አንስቷል።

በክልሉ በሕገ መንግሥታዊ አግባብ እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የፌደራል መንግሥትም አጥፊው ቡድን በቀሰቀሰው ግጭት የደረሰውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም እየሠራ እንደሚገኝም አስረድቷል።

ይህ የመልሶ ግንባታና የማቋቋም ሥራ የሁሉንም ርብርብ እና እገዛ የሚጠይቅ ነው ያለው መንግስት፥ ለዚህም መላው ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡንም አስታውሷል።

የደረሰውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ለመቀነስ እና ክልሉን በተሻለ የአስተዳደር እና የልማት ቁመና ላይ ለማድረስ የማይተካ ሚና ካላቸው ተዋንያን ዋነኛዎቹ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸውም ነው ያለው።

ከእነዚህ ዜጎች አንዳንዶቹ በሕወሓት ፕሮፖጋንዳም ሆነ በሕገ ወጡ ቡድን አስገዳጅነት ነፍጥ አንግበው በውጊያ ሜዳ ላይ እስከመሰለፍ መድረሳቸውንም ገልጿል፡፡

ነገር ግን እነዚህ የክልሉ ተወላጆች ዋነኛው የጥፋቱ ጠንሳሽ እና ባለቤት አለመሆናቸውን መንግሥት ይገነዘባል ያለው መግለጫው፥ ከዝርፊያው እና ከምዝበራው ተካፋይ ያልነበሩ፣ ሀገራቸውን የሚወዱ የክልሉ ተወላጆች በአጥፊው ቡድን ጎትጓችነት እና ቅስቀሳ ከመንግሥት ጋር ተቃርነው፣ መሣሪያ ታጥቀው የተሰለፉ ቢሆንም እንኳን መንግሥት ነገሩን በሆደ ሰፊነት ማየት እንደሚገባው ያምናልም ብሏል።

በመሆኑም የሀገር አንድነትን ለማጠናከር እና አጥፊው ቡድን ያፈረሳቸውን የጋራ እሴቶችን፣ አብሮነትን እና መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የተለያዩ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን መንግሥት እንደሚያምንም ጠቅሷል፡፡

በመሆኑም፣ በሕገ ወጥ ጥቃቱ እና ተያያዥ በሆኑ የወንጀል ተግባራት ጉልህ ተሳትፎ አላቸው ተብለው ከተጠረጠሩ እና በዚህ መነሻ የፍርድ ቤት መያዣ ከወጣባቸው ከፍተኛ የሕወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በስተቀር ሌሎች ዜጎች ያለ ሥጋት ወደ ቀደመው ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ፤ ይህንንም እውን ለማድረግ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው እና መኖሪያቸው በመመለስ ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉም ጥሪውም አቅርቧል።

በዚህ መንገድ ከአጥፊው ቡድን ተለይተው ወደሰላማዊ ኑሯቸው የሚመለሱ የክልሉ ተወላጅ ዜጎች፣ የትኛውም የሕግ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው፣ ከአጥፊ ተግባራት ተቆጥበው፣ ወደ ሥራቸው እና ኑሯቸው በሰላም መሠማራት እንደሚችሉም ነው አንስቷል።

እነዚህን ዜጎች በመልካም ሁኔታ በመቀበል እንዲተባበሩ እና የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ለሚመለከታቸው የጸጥታ፣ የአስተዳደር እና የሕግ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊው መመሪያ መሰጠቱንም ነው የገለጸው።

የጥፋት ቡድኑ አካል ሆነው በተፈጸመው ወንጀል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ፣ የፍርድ ቤት መያዣም የወጣባቸው ከፍተኛ የሕወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች፣ በሰላም እጃቸውን ለሕግ አስከባሪ ተቋማት እንዲሰጡም መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።

እነዚህ አመራሮች እስከዛሬ ከደረሰው ሀገራዊ ጥፋት እና ጉዳት በመማር፣ ለፍትሕ ራሳቸውን በማቅረብ፣ ተጨማሪ ሀገራዊ ኪሣራ እንዳይደርስ እና በከንቱ የዜጎች ደም እንዳይፈስ የበኩላቸውን በጎ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ነው መንግሥት ጥሪ ያቀረበው።

ይህንን የሚያደርጉ ከፍተኛ የሕወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ራሳቸውን ከከፋ ቅጣት፣ ወገናቸውን ከመጎሳቆል ይታደጉታል ሲልም ነው ጥሪው ያቀረበው፡፡

ይህንን የመጨረሻ ጥሪ ተጠቅመው ራሳቸውን ለፍትሕ በማያቀርቡ የሕወሓት ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ ግን ሕግ በሚፈቅደው ሁሉም ዓይነት መንገድ፣ ሕግ ለማስከበር ሲባል፣ አስፈላጊው ሁሉ የሚፈጸም ይሆኗል ብሏል መንግስት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.