Fana: At a Speed of Life!

ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ የሚውሉ ስድስት አዳዲስ የትራፊክ መስመሮች ተግባራዊ ሊደረጉ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመዲናዋ ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ የሚውሉ አዳዲስ የትራፊክ መስመሮች ተግባራዊ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ስድስት መስመሮች እና አራት ነባር መስመሮች ከመነሻ እስከ መዳረሻ እንዲራዘሙ ይደረጋል ተብሏል ፡፡
በዚህም ከፒያሳ – ዊንጌት – ሳንሱሲ፣ ከጦር ኃይሎች – አየር ጤና፣ ከቅዱስ እስጢፋኖስ – አራት ኪሎ – ሽሮ ሜዳ፣ ከመገናኛ – ሾላ – ቀበና – 6 ኪሎ፣ ከመገናኛ – ሾላ – ቀበና – አራት ኪሎ እና ከከዛንቺስ – ብሄራዊ ባሉት መንገዶች የአውቶቡስ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ መስመሮች እንደሚዘጋጅ ቢሮው ገልጿል ።
ከሜክሲኮ – ሳርቤት – ጀርመን አደባባይ – ጀሞ፣ ከሜክሲኮ – ሳርቤት – ጀርመን አደባባይ – ኃይሌ ጋርመንት፣ ከመገናኛ – ላምበረት – ሳራ አምፖል እና ከሜክሲኮ – ፒያሳ – አዲሱ ገበያ ነባር መስመሮች ከመነሻ እስከ መዳረሻ ተግባራዊ መደረጉን ቢሮው ገልጿል፡፡
ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ የሚያገለግሉ መስመሮች መጀመራቸው የብዙሃን ትራንስፖርት ምልልስ መጠኑን ከፍ በማድረግ አገልግሎትን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ሲሆን የትራፊክ መጨናነቅንና የተሽከርካሪ ግጭትን መቀነስ አስችሏል ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም በከተማዋ ተግባራዊ በተደረጉ የአውቶቡስ ብቻ መስመሮች የሚባክነው ጊዜ በአማካይ በ23 ደቂቃ ማሻሻል አስችለዋል፡፡
በተያያዘ በመንገዱ ላይ በሰዓት በአማካይ 34 እና ከዚያ በላይ የብዙሀን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን እና በመንገዱ ላይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚጓጓዘው ተሳፋሪ ብዛት ከ202 ሺህ 300 በላይ እንደመስፈርት መቀመጡን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.