Fana: At a Speed of Life!

የምርጫ ጉዳዮች ብቻ የሚዳኙባቸው 21 ችሎቶች መደራጀታቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምርጫውን ተከትሎ ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ ክርክሮች በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱበት ረቂቅ ደንብ ላይ የአስረጂዎች መድረክ ተካሔደ።

በዚህ ዓመት የሚካሔደውን 6ኛውን አገራዊ የምርጫ ሒደት ተከትሎ የሚነሱ ክርክሮችን በልዩ ሁኔታ የሚያስተናግዱ ፍርድ ቤቶች እየተደራጁ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት የሚስተናገዱባቸው የስነ-ስርዓትና የማስረጃ ደንብ ቁጥር 1/2013 አስመልክቶ በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የአስረጂዎች መድረክ ተካሒዷል።

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የፌዴራል  ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ አቶ ተስፋዬ ንዋይ በሀገሪቷ ምርጫን በበላይነት የሚመራው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን

ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚቻል በአዋጅ መደንገጉን ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎም ለሚነሱ ክርክሮች አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት የሚያስችሉ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

ረቂቅ ደንቡ የመራጮችና የዕጩዎች ምዝግባ፣ የስነ-ምግባር ጥሰት፣ የድምፅ አሰጣጥና ቆጠራን አስመልክቶ  ለሚነሱ ክርክሮች ፈጣን ውሳኔን መስጠት የሚያስችሉ አካሔዶችን ማስቀመጡን ጠቁመዋል።

አሁን ባለው የመደበኛ ፍርድ ቤት የክርክር ሒደት የምርጫን ጉዳይ በሚፈለገው መልኩ ውሳኔ መስጠት ስለማይቻል ፍጥነትና ቅልጥፍናን ታሳቢ ያደረገ የስነ-ስርዓት ሕግና ደንብ እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ረቂቅ ደንቡ ካካተታቸው ጉዳዩች መካከል ፍርድ ቤቶቹ በቀረቡላቸው የምርጫ ክርክሮች ላይ የሚሰጡት ውሳኔ የይግባኝ ስርዓት የሌላቸውና የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሆኑም ማስቀመጡን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቶቹ የምርጫ ጉዳይ ክርክሮችን ቅዳሜና እሑድ እንዲሁም በሕዝብ በዓላት ቀን ጭምር  የሚያስተናግዱ እንዲሆን ይደነግጋል ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ።

ረቂቅ ደንቡ በክርክር ወቅት የሚቀርቡ የክስ፣ የመልስና የማስረጃ አቀራረብ ሒደትም መከተል የሚገባቸውን ስነ ስርዓት ማመላከቱንም ጠቅሰዋል።

የምርጫ ጉዳዮች ብቻ የሚዳኙባቸው 10 ችሎቶች በከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ 11 ችሎቶች ደግሞ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስር መደራጀታቸውንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም በምርጫ ሂደት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ብዛትና አይነት በማየት ተጨማሪ ችሎቶች እንዲደራጁ ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብባቢ አቶ አቡ በርኪ የስነ-ስርዓትና የማስረጃ ረቂቅ ደንቡ ላይ የሚካተቱ ጉዳዮች በፍጥነት እንዲካተቱና ለምክር ቤቱ ቀርበው እንዲፀድቁ  አሳስበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.