Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ትክክለኛ መሆኑን በኢትዮጵያ የቀድሞው የእስራኤል አምባሳደር ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን በኢትዮጵያ የቀድሞው የእስራኤል አምባሳደር አቪ ግራኖ ገለጹ፡፡

አቪ ግራኖት ከኢትዮጵያ ጋር ስላላቸው ትስስር እና ስለ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ በእስራኤል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ፋሲል ለገሰ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ትክክለኛ መሆኑን በመጥቀስ፥ በኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተጀመረው ለውጥ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተግባራት እና የመንግሥታቸውን እንቅስቃሴ በቅርብ እንድሚከታተሉ በመጥቀስም፥ በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት ምን ያህል በጥንቃቄ እንደሚሰሩ መረዳት ችያለሁም ነው ያሉት፡፡

አልፎ አልፎ የሚታየው አንዳንድ ተግዳሮት በዴሞክራሲ ለውጥ ሥርዓት የሚያጋጥም ስለሆነ መደናገጥ እንደማያስፈልግም አንስተዋል፡፡

አያይዘውም “በእኔ አመለካከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዴሞክራሲ እንነጋገር፣ ምርጫ ተወዳደሩ፣ በሀሳብ እንፎካከር፣ በፍትህ እንዳኝ፣ ጦርነት ለማንም አይበጅም በማለት ነው ሁሉን የጋበዙት” ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በሃገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት በተዘረጋበት እና አዳዲስ ለውጦች በተጀመሩበት ሁኔታ የሀሳብ ልዩነት በምርጫ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ መስተናገድ እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለስለስ ያሉ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን መጠቀም ሁሉንም በትዕግሰት ለማስተናገድ ጥረት ማድረጋቸውን አድንቀዋል፡፡

ህወሓት በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙ ወንጀል መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፥ እንዲህ አይነት የሕገ-መንግሥት ጥሰት በሚፈጽሙትና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ ስህተቶች በዝምታ የማይታለፉ መሆናቸውን የእስራኤልን ታሪክ በመጥቀስ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር አቪ በኢትዮጵያ ያሉ ሂደቶችን በቅርብ እንደሚከታተሉ ገልፀው ለሚታዩ አለመግባባቶች መፍትሄው ዴሞክራዊ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

አምባሳደር አቪ ግራኖት ከፈረንጆቹ 1995 እስከ 1998 ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፥ አሁን ላይ በእስራኤል እና አፍሪካ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር የሚሠራው የአፍሪካ እስራኤል የንግድ ምክር ቤት ሥራ አመራር አባል በመሆን ያገለግላሉ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.