Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል እየተደረገ ከሚገኘው ድጋፍ 70 በመቶው በመንግስት የተሸፈነ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በትግራይ ክልል እየተደረገ ከሚገኘው ድጋፍ 70 በመቶው በመንግስት የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው የአጋር አካላት ድርሻ መሆኑንብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

በትግራይ ክልል ለ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ሕዝብ በመንግስትና በአጋር አካላት ሠብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በስምንት መጋዘኖች በቂ የመጠባበቂያ ምግብ ክምች መኖሩንና የ3 ሚሊየን ኩንታል እህል ግዥ መፈፀሙንም አስታውቋል።

በእስካሁን ሒደት 1 ነጥብ 94 ቢሊየን ብር ግምት ያለው 841 ሺህ 250 ኩንታል የምግብ እህል በቅንጅት  መሰራጨቱን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ለ128 ሺህ 535 ቤተሰቦች 246 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶቸም ተሰራጭተዋል ብለዋል።

በክልሉ የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ሠላም ከሚያስከብሩ አካላት ጋር በመተባበር ድጋፉን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን መንግስት እርዳታውን በማከፋፈል ከፍተኛውን ድርሻ ቢወስድም ከአጋር አካላት የሚጠበቀው ድጋፍ በሚፈለገው ፍጥነት ባለመድረሱ ጊዜያዊ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ገልፀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ለእናቶች፣ ለሕፃናትና ለነፍሰጡሮች የሚቀርበው አልሚ ምግብ የዋጋ ውድነትን ተከትሎ እጥረት በመኖሩ ተጨማሪ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ያም ሆኖ መንግስት ባሉት ስምንት መጋዘኖች በቂ የመጠባበቂያ ምግብ ክምች ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞን በስድስት ወረዳዎች ለሚገኙ 104 ሺህ 955 ተፈናቃይ ወገኖች ስንዴ፣ አልሚ ምግብ፣ የምግብ ዘይትና የበቆሎ ዱቄት ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

በአማራ ክልል አዊ ዞን ተጠልለው ለሚገኙ ከ97 ሺህ በላይ ዜጎችም እንዲሁ የዕለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገ ሲሆን ከ27 ሺህ ኩንታል በላይ እህል በሁለት ዙር እንዲከፋፈል መደረጉን ጠቁመዋል።

መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ከሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ልምድ በመውሰዱ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች እርዳታ የማድረሱን ስራ እንዲቀል ማድረጉንም አቶ ደበበ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከድጋፍ ስራው ጎን ለጎን ከሌሎች ሴክተሮች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን፤ በዋናነትም በጤና፣ በትምህርት፣ በውሃ አቅርቦትና በግብርና መስኮች የሕብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟሏትና ድጋፉን ለማጠናከር የላቀ ትኩረት መስጠቱን አቶ ደበበ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.