Fana: At a Speed of Life!

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ዘርፍ የግል ባለሃብቶች የሚሰማሩባቸው 44 ፕሮጀክቶች ተለይተዋል-የትራንስፖርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በግል ባለሃብቶች እና በመንግስት እና በግል ባለሃብቶች ጥምረት ሊካሄዱ የሚችሉ 44 ፕሮጀክቶች መለየታቸውን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለፁ።
ፕሮጀክቶቹ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፍ የአዋጭነት ጥናት የተጠናቀቀላቸው ናቸው ተብሏል።
ሚኒስትሯ ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የትራንስፖርት ኢንቨስትመንት ጉባኤ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ጉባኤው ከነገ በስቲያ እና ሃሙስ የሚካሄድ ሲሆን የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደ ተቋም የተዘጋጀው የ10 አመት መሪ እቅድም ከዚሁ መርሃ ግብር ጋር የተጣጣመ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ 44 ያህል ፕሮጀክቶች በመንገድ ልማት፣ በመንገድ ትራንስፖርት፣ በሎጂስቲክስ፣ በባቡርና በአየር ትራንስፖርት መስኮች መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር ሊጣመር በሚችልባቸው እድሎች ላይ ምክክር ይደረጋልም ነው የተባለው፡፡
የኢንቨስትመንት አዋጁ ባለፈው አመት መሻሻሉን ተከትሎ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፍ የግል ባለሃብቶች በተናጠል እና ከመንግስት ጋር ተጣምረው የሚሰማሩባቸው ዘርፎች ተለይተዋል።
44ቱ ፕሮጀክቶችም በመንገድ ልማት፣ በሎጂስቲክ፣ በትራንስፖርት፣ በባቡርና በአየር ትራንስፖርት መስኮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ነው ሚኒስትሯ ያነሱት።
300 የሚጠጉ የዘርፉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አልሚዎችም በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ተጠቃሚ በሚሆኑበት ሁኔታ ዙሪያ በሚያተኩረው ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
ከፍላጎት እና አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሰፊ ችግሮች የሚስተዋልበት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ዘርፍ ቀልጣፋ እና ውጤታማ ይሆን ዘንድ በመንግስት ብቻ የተያዙ ስራዎች የግል ባለሃብቶች እንዲገቡበት መፈቀዱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ በመግለጫቸው።
በፋሲካው ታደሰ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.