Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ ሀሰተኛ የመረጃ ምንጮችንና መረጃውን የሚያሰራጩ አካላትን ለህግ ማቅረብ እንደሚገባ አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ ሀሰተኛ የመረጃ ምንጮችን፣ መረጃውን የሚያሰራጩ እና ሆን ብለው መረጃውን ተቀብለው የሚያናፍሱ አካላትን ለህግ ማቅረብ እንደሚገባ አስታወቁ፡፡

ምክትል ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም ጠል የሆኑ ቡድኖች ሆን ብለው በከተማዋ ያለውን አብሮነት ለማናጋት ፣ ህዝብን ለማሸበር፣ ለማጋጨት እና የሰላም ስጋት ለመፍጠር የያዙትን ሃሳብ ለማስፈጸም “ብሄር እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የማጥቃት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው “የሚል ሀሰተኛ መረጃ እና ፕሮፖጋንዳ እያሰራጩ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል “በከተማው ሰላም የለም” ብለው ፕሮፖጋንዳ እያሰራጩ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እነዚህ ሃሰተኛ መረጃዎች በስፋት የተሰራጩ በመሆኑ በነዋሪው ላይ አሉታዊ የስነ ልቦና ጫና እያሳደሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ፖሊስ እና የከተማው ጸጥታ አካላት ሀሰተኛ የመረጃ ምንጮችን ፣ መረጃውን የሚያሰራጩትን እንዲሁም ሆን ብለው መረጃውን ተቀብለው የሚያናፍሱ አካላትን ተከታትለው ለህግ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪያዎችም ይህን በመረዳት እና ከሃሰት መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅ እና በሃሰት መረጃው ፍፁም ሳይደናገጡ መረጃውን የሚያናፍሱ አካላትን ለፖሊስ እና ለጸጥታ አካላት በማጋለጥ እያበረከቱ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.