Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የ200 ሚሊየን ብር የቦንድ ግዢ ፈፀመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የ200 ሚሊየን ብር ቦንድ ግዢ ፈጽሟል፡፡

ባንኩ የቦንድ ግዢውን የፈጸመው በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ፍቃዱ ደግፌን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በማስጀመሪያው ላይ ተገኝተዋል፡፡

ምክትል ገዢው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላ ሀገሪቱ ባሉት በርካታ ቅርንጫፎች ቦንድ በመሸጥ ህብረተሰቡ ለግድቡ ድጋፍ እንዲያደርግና የቁጠባ ባህሉን እንዲያዳብር ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡

ከመጋቢት 15 እስከ 25 ቀን በሚደረገው መርሀ ግብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቅርንጫፎች እንዲሁም ድንኳኖችን በመትከል ከ50 ብር ጀምሮ የቦንድ ሽያጭ እንደሚካሄድ አቶ በፍቃዱ ገልፀው ህብረተሰቡ ቦንድ በመግዛት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ በድጋሜ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቦንዱን ያስረከቡት የባንክ የቅርንጫፍ እና የዲጂታል ባንኪንግ ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፍቅረሥላሴ ዘውዱ ባንኩ ለግድቡ ዋነኛ የፋይናንስ አቅራቢ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን የ101 ቢሊየን ብር የፋይናንስ አቅርቦት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ላበረከተው አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

እንደ ሀገር የሚጠበቅበትን የሚወጣ ባንክ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ግድቡ ግንባታ የሉአላዊነትና የፍትሀዊነት ጥያቄ፣ የአንድነት ጉዳይ እና ወደተደላደለ እድገት አሻጋሪ ፕሮጀክት መሆኑንን ተናግረዋል፡

ፕሮጀክቱ እንዲከሽፍ በውስጥም በውጪም ያሉ ተቃራኒ ሀይሎች እየተፈታተኑን ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ያለንበት ሁኔታ በጣም ከባድ ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ ትብራችንን ልክ አያቶቻችን እንዳደረጉትና አድዋ ላይ የውጭ ወራራ ኃይልን እንደመከቱት ይህንንም በተመሳሳይ ለማሸነፍ መዘጋጀት አለብን ብለዋል፡፡

በርትተን ግድቡን እንደጀመርነው እንጨርሰዋለንም ነው ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.