Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ የአፋር ክልል የምርጫ ጣቢያ ዝርዝርን አስመልክቶ ባቀረበው አቤቱታ ላይ ውሳኔ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የምርጫ ጣቢያ ዝርዝርን አስመልክቶ ያቀረበው አቤቱታ ላይ ውሳኔ ሰጠ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ይፋ መሆንን ተከትሎ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የምርጫ ጣቢያዎች ያለአግባብ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል መንግስት ስር በሚገኙ ቀበሌዎች ስም ይፋ ተደርገዋል የሚል አቤቱታ ለቦርዱ እንደቀረበ እና የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት አቤቱታውን ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ ማሳወቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ጣቢያዎችን ሲያደራጅ በአቅራቢያው ያሉ ዜጎች በመራጭነት ለመመዝገብ እንዲሁም ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማስቻል በማሰብ ሲሆን የምርጫ ጣቢያዎች አደረጃጀትም ባለፉት 5 አጠቃላይ ምርጫዎች ተመሳሳይ መስፈርቶችን በመጠቀም ሲከናወን የቆየ ነው።

ቦርዱ ለስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በሚዘጋጅበት ወቅት በ2007 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ የተጠቀመባቸውን የምርጫ ጣቢያዎችን ታሳቢ በማድረግ በሁሉም ምርጫ በሚደረግባቸው የሃገሪቱ ክልሎች ተገማች የመራጮች ቁጥርን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጁ ናቸው።

እንደሚታወቀው ምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች ድምጻቸውን ለመስጠት የሚመቻቹ የመመዝገቢያ እና ድምጽ መስጫ ቦታዎች ሲሆኑ የየትኛውም የመንግስት አስተዳድር መዋቅር አካላት አይደሉም።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በሚያከናውናቸው የምርጫ ኦፕሬሽን ተግባራት በተለያዩ ደረጃዎች የራሱን መዋቅር የሚያዘጋጅ ሲሆን እነዚህ መዋቅሮች ከመንግሰት ቋሚ መዋቅር ጋር ተመሳሳይነት የላቸውም።

ቦርዱ ከላይ የተጠቀሱትን ጥሬ ሃቆች እና አሰራሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የቀረበውን የምርጫ ክልሎች አላግባብ በሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ተጠርተዋል የሚለውን የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የቀረበውን አቤቱታ መርምሯል።

ምንም እንኳን ከላይ እንደተጠቀሰው ቦርዱ በ2007 ዓ.ም የተጠቀመበትን የመረጃ ዝርዝር ለስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ቢጠቀምም፣ የምርጫ ጣቢያዎች የአስተዳደር ወሰኖችን የሚወስኑ መገለጫዎች ባይሆኑም ቦርዱ ምርጫ በምንም መልኩ የሰላም መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆን በማሰብ

  • በጋላእቶ/አዳይሌ
  • በአዳይቱ/አዳይቱ
  • በቴውኦ/አላሌ
  • በጉርሙዳሊ/ዳንሌሄላይ
  • በኡንዳፎኦ/ኡንዱፎ
  • በጋዳማይቱ/ጋርባኢሴ
  • በአፍዓሶ/አፉአሴ
  • በባላእቲ ጎና/መደኒ

ቀበሌዎች ሊከፈቱ የነበሩትን 30 የምርጫ ጣቢያዎች በአካባቢው እንዳይቋቋሙ ወስኗል።

በዚህም መሰረት በአካባቢው የሚኖሩ እና የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ መስጠት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ዜጎች በአቅራቢያቸው ባለ ሌላ ቀበሌ መመዝገብ እና ድምጻቸውን መስጠት የሚችሉ ሲሆን ይህንን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ቦርዱ ለምርጫ አስፈጻሚዎቹ ተገቢውን መመሪያ የሚያስተላልፍ ይሆናል።

ይህ ውሳኔ የምርጫ ሰላምን ቅድሚያ በመስጠት በቦርዱ የተወሰነ ሲሆን የመራጮችን የመምረጥ መብት በማይገድብ መልኩ እንዲፈጸም ያደርጋል።

በዚህ አጋጣሚም ቦርዱ ሌሎች አካላት የምርጫ ኦፕሬሽንን የምርጫ ጣቢያዎች እና የምርጫ ክልል ቢሮዎችን አከፋፈት ለቆዩ የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግቦች ግብአት ከመጠቀም እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.