Fana: At a Speed of Life!

በስልጤ ዞን አሊቾ ውሪሮ ወረዳ በደረሰ የእሳት አደጋ 60 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ንብረት ወደመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልጤ ዞን አሊቾ ውሪሮ ወረዳ በደረሰ የእሳት አደጋ 60 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ንብረት መውደሙ ተገለጸ።

በአደጋው ከ70 በላይ ቤቶች የወደሙ ሲሆን ከ450 በላይ ቤተሰቦች ለጉዳት መዳረጋቸውም ተመልክቷል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አብዱልዋሪስ ጀማል አደጋው በደረሰበት ቡኔ ሳቀሞ ቀበሌ ተገኝተው ተጎጂ ቤተሰቦችን አጽናንተዋል።

በትናንትናው ዕለት 8 ሰዓት አካባቢ በደረሰው አደጋ 78 መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል ከ450 በላይ ቤተሰቦች የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል ብለዋል አቶ አብዱልዋሪስ ።

በዚህ አደጋ 60 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ንብረት መውደሙን የገለጹት አቶ አብድልዋሪስ ለተጎጂ ቤተሰቦች በጊዜያዊነት ብርድልብስ፣ የስንዴ ዱቈትና ሸራ መቅረቡንና በቋሚነት ለማቋቋምም ከሚመለከተው ጋር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሸምሴ ኑሪ በበኩላቸው የተጎዱ ቤተሰቦችን ጊዜያዊ መጠለያ ተዘጋጅቶ ምግብና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች እየቀረቡ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቋሚነት ማቋቋም እንዲቻል በወረዳውና ከወረዳው ውጪ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያስተባብር ቋሚ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስረድተዋል።

በወረዳ የሳር ክዳን ቤቶች በብዛት እንደሚገኙ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ቀጣይም የዚህ አይነት አስከፊ አደጋ እንዳይደርስ ህብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ የግንዛቤ ስራ ይሰራል ብለዋል።

ለዚህም ማህበረሰቡ አጋዥ ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን ሰበሃዲ ሸውሞሎ የወረዳው ፖሊስ ስለ አደጋው መረጃ እንደደረሰው ስፍራው ላይ ተገኝቶ  የአደጋውን መንሴ ለማጣራ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

እስካሁን ባደረጉት ምርመራም የኤሌክትሪክ ገመዶች በፈጠሩት ኮንታክት የተነሳ እሳት ነው የሚል መነሻ መረጃዎችን ማሰባሰባቸውን ጠቁመዋል።

ቤተሰብ የምናስተዳድርበት ቋሚ ንብረታችን የሆነው እንሰት በአደጋው በመውደሙ በእጅጉ አሳስቦናል ያሉት ነዋሪዎቹ መንግስት ፈጥኖ ሊደርስልን ይገባል ሲሉም ጥሪ ማቅረባቸውን የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አስታውቋል።ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.