Fana: At a Speed of Life!

ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የዕውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር እሑድ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአፍሪካ ብሎም ለኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ በ10 ሺህ ሜትር በባርሴሎና የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት ለሆነች ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የዕውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር እሑድ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህንን ያስታወቀው ከተለያዩ አካላት የተውጣጣው ብሄራዊ ኮሚቴ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

መግለጫውን የሰጡት የኮሚቴው አባል የሆኑት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛህኝ አበራ ፣ የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ  እና የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አቶ ነጋ ቱጁባ ናቸው፡፡

በአትሌቲክሱ ዘርፍ ኮ/ር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች፡-

እ.ኤ.አ በ1992 የባርሴሎና ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በ10,000 ሜትር ውድድር በመወከል በሴቶች ለኢትዮጵያ፣ እንዲሁም ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ማስመዝገብ ችላለች፤

ከዚህ ውጤት በኋላ በኦሊምፒኮች፣ በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች፣ በአለም አገር አቋራጭ ውድድሮች፣ በኮንቲኔንታል ካፕ፣ ከ20 አመት በታች የአለም ሻምፒዮና፣ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች፣ በአለም አትሌቲክስ ፋይናል፣ በጎልደን ሊግ፣ በኢንተርናሽናል ማራቶን እና በኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ሻምፒዮናዎች ከ13 በላይ ወርቆች፣ 2 ብሮች፣ 1 ነሃስና 3 ዲፕሎማዎችን ለሃገሯ አበርክታለች፤

በኢንቨስትመንት ረገድ፡- 

ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርታ በተለያዩ አካባቢዎች ሆቴልና መዝናኛዎችን ገንብታ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠር ችላለች፤

በተቋም አመራርና በኃላፊነት ቦታዎችም፡- 

ኮ/ር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ቤተሰባዊ ህይወትን ከመምራት እና በማህበራዊ ጉዳዮች ከመሳተፍ ጎን ለጎን በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን የካውንስል አባል፣ በምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ዞን ደግሞ ም/ፕሬዝዳንት፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአትሌቶች ተወካይነት ጀምሮ በተቀዳሚ ም/ፕሬዝዳንትነትና በፕሬዚዳንትነት እያገለገለች እንደምትገኝ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.