Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ማር ለመቁረጥና የእርሻ መሬትን ለማስፋፋት በሚደረግ እንቅስቃሴ በደን ሀብቶች ላይ ውድመት እየደረሰ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ማር ለመቁረጥ፣ የእርሻ መሬትን ለማስፋፋት፣ ከሰል ለማክሰልና አዲስ የመኖ ሳር ለማብቀል በሚደረግ እንቅስቃሴ በደን ሀብቶች ላይ ውድመት እየደረሰ መሆኑን የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ፣ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ግጄ እንዳሉት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከየካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ የእሳት ቃጠሎዎች ተከስተዋል፡

በዚህም በብዝሃ ህይወትና በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት፡፡

በከፋ፣ በጉራጌ፣ በጋሞ፣ በጎፋና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም በኮንታ ልዩ ወረዳ ሰደድ እሳት የተነሳ ሲሆን በተለይም በጉራጌና ከፋ ዞኖች የተከሰቱ ቃጠሎዎች እስካሁን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር እንዳልዋሉም ተናግረዋል።

እሳቱ በከፋ ዞን አዲዮ ወረዳ በሰፊ ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን ላይ ጉዳት ሲያደርስ በጉራጌ ዞንም በሶዶ አካባቢና በጊቤ ፓርክ አካባቢ ደን ማቃጠሉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በማዜ ብሄራዊ ፓርክ ላይም ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበር ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ቃጠሎው የ40 እና 50 አመት የደን ሀብቶችን ከማውደም ባለፈ የውሃ አካላትን የሚያደርቅና የሚበክል፣ እንዲሁም አፈር እንዲሸረሸር የሚያደርግ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተቀናጅቶ አደጋውን እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል ።

ከቀጣዩ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር በተያያዘም በክልሉ ከ730 ሚሊየን በላይ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በቢቂላ ቱፋ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.