Fana: At a Speed of Life!

የ2013 ምርጫ ነጻ የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ አምድ ድልድል ለፖለቲካ ፓርቲዎች ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2013 ምርጫ ነጻ የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ አምድ ድልድል ለፖለቲካ ፓርቲዎች ቀረበ።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

በዚህ ወቅትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ባሉበት ሆነው የመራጮች ምዝገባ ማድረግ የሚችሉበት የቀጥታ (ኦንላይን) የመራጮች ምዝገባ ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ውይይቱ የእስካሁኑን ሂደት የሚገመግም እና ቀጣይ ስራዎች ላይ ያተኮረ ነው።

እስካሁን የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠናን በተመለከተም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ቦርዱ ባወጣው እቅድ መሰረት ከሞላ ጎደል ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አብራርተዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም በ610 የምርጫ ጣቢያዎች 100 ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ተሰጥቷቸዋልም ተብሏል።

በጸጥታ ችግር ምክንያት መተከልና ካማሽ ዞን ስልጠናው አልተሰጠም ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሌሎች አካባቢዎች በስፍራው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ቦርዱ መረጃ እስከሚደርሰው እየጠበቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልልም ከሰሞኑ የጸጥታ ችግር በተፈጠረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ስልጠናው ያልተሰጣቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ካለው የጸጥታ ችግር ባለፈም የትራንስፖርት ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰው፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ በጋምቤላ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ አለመጀመሩን ገልጸዋል።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የድርጊት መርሃ ግብር መሰረት መራጮች ምዝገባ ከትናንት በስቲያ ተጀምሯል።

በምስክር ስናፍቅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.