Fana: At a Speed of Life!

የቀጣዩ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል።
 
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ነሃሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም የድምጽ መስጫ ቀን እንዲሆን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።/span>
 
የቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ የባለድርሻ አካላት ስብሰባ በጁፒተር ሆቴል ተካሂዷል።
 
በስብሰባው የመጭው ሃገራዊ ምርጫ አጠቃላይ የትግበራ መርሃ ግብር ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን፥ የጊዜ ሰሌዳው ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ምርጫውን ለማስፈጸም ታቅዶ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
 
በዚህም ከታህሳስ 22 እስከ መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ማደራጃ፣ የካቲት 24 የምርጫ ክልል ካርታ ይፋ ማድረጊያ፣ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የመራጮች ምዝገባ እንዲካሄድ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ቀርቧል።
 
ከዚህ ባለፈም የመወዳደሪያ ምልክት ማቅረቢያና መወሰኛ ጊዜ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 8 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የዕጩ ምዝገባ ጊዜ ከሚያዚያ 13 እስከ ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የምረጡኝ ዘመቻ ከሚያዚያ 27 እስከ ነሃሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሁም የዕጩዎች ዝርዝር ይፋ ማድረጊያ ሰኔ 7 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሆን ረቂቅ ቀርቦ ምክክር እየተደረገበት ነው።
 
የድምጽ መስጫ ቀን እና ውጤት ሂደትን አስመልክቶ ለመራጮች መረጃ የሚሰጥበት ጊዜ ከሰኔ 24 እስከ ነሃሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ፣ ዘመቻ የሚከለከልበት ጊዜ ከነሃሴ 6 እስከ ነሃሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የድምጽ መስጫ ቀን ነሃሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሁም የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያዎች ይፋ የሚደረግበት ቀን ነሃሴ 10 እና 11 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሆን በቀረበው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ባለድርሻ አካላት ምክክር እያደረጉበት ይገኛል።
 
ከዚህ ባለፈም በምርጫ ክልል ደረጃ ውጤት ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ከነሃሴ 11 እስከ ነሃሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሁም የቦርዱ የተረገጋጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜ ከነሃሴ 11 እስከ ነሃሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ሆኖ ቀርቧል።
 
በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው እና አፈፃፀሙ ላይ እየተካሄደ ባለው ውይይት የመራጮች ምዝገባ ጊዜ 30 ቀናት መሆኑ እና የእጩ ምዝገባ ቀናት አንሰዋል የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
 
በተጨማሪም “የድምፅ መስጫ ቀኑ ክረምት ላይ መዋሉ ለማስፈፀም ያስቸግራል፤ ጥቅምት ወይም ህዳር ወር ላይ ቢሆን፣ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ወከባ እንዳይፈጠርስ ቦርዱ ምን ዝግጅት አድርጓል?” በሚልም ጥያቄ ቀርቧል።
 
በተጨማሪም “የምረጡኝ ቅስቀሳ ቀናት እንደሚያንሱ እና ከወዲሁ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎች አሉና ቦርዱ ይህን እንዴት ይመለከተዋል?” የሚሉና “ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ የሚደረደሩበት ቅደም ተከተል በእጣ ይሆናል ማለት ምን ማለት ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።
 
ቦርዱም በእነዚህ እና ሌሎች ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
 
በምላሽና ማብራሪያውም የመራጮች ምዝገባ በህግ የተቀመጠው 30 ቀን መሆኑን ነው ያስታወቀው።
 
የእጩ ምዝገባ ቀናትን በተመለከተም አስፈላጊ ከሆነ ቀናት መጨመሩን ቦርዱ ሊያየው እንደሚችል ነገር ግን በእቅዱ ላይ የተቀመጠው ቀን ለፓርቲዎች እንደማያንስ እና እንደውም ጫና የሚሆነው ቦርዱ ላይ መሆኑን አስረድቷል።
 
ነሃሴ ላይ ምርጫው መካሄዱ ቦርዱ ወዶ የገባበት እንዳልሆነና ግንቦት ለማድረግ ስላልተቻለ መሆኑን በማስረዳት ወደ ነሃሴ መወሰዱን ገልጿል።
 
አፈፃፀሙ ክረምት በመሆኑ ብዙ ችግር እንደሚገጥመው እሙን መሆኑን በማንሳት ከክልል መንግስታት፣ ከፌደራል መንግስትና ሌሎች ተቋማት ቦርዱ የሎጀስቲክስ ድጋፍ ጠይቆ ለማስፈፀም ግን ጥረት እንደሚያደርግ ነው ያመለከተው።
 
ከመስከረም ካለፈ ግን የህግ ጥሰት የሚፈጠር በመሆኑ ወደፊት መግፋት እንዳልተቻለ አስታውቋል።
 
የዘመቻ ጊዜ ከወከባ እና ችግር እንዳይኖር በማድረጉ ረገድ ከዚህ በፊት ፓርቲዎች ችግር ሲገጥማቸው ቦርዱ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን በማንሳት አሁን ይህንን ድጋፍ ለማስፋት በምርጫ ዘመቻ ወቅት የራሱ ዴስክ አዘጋጅቶ ተቋማዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።
 
የምረጡኝ ቅስቅሳ አሁን መጀመር እንደማይቻል ያስታወቀው ቦርዱ፥ የተሰጠው ሶስት ወር ግን በቂ መሆኑን አመልክቷል።
 
ከአሁኑ ቅስቀሳ የጀመሩ አሉ ለተባለው ውይይት እና ንግግር ከህዝብ ጋር ማደረግ እንደሚችሉ ነገር ግን እኔን ምረጡኝ የሚል ዘመቻ መጀመር እንደማይቻልና ያንን የሚያደርጉ ፓርቲዎች ላይ ቦርዱ ማጣራት እንደሚያደርግ ነው ያስታወቀው።
 
ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀት ቅደም ተከተል ሲባል የሚደረደሩበት መንገድ በእጣ የሚወሰን ይሆናል እንጂ ከዚህ በፊት እንደነበረው አይሆንም ነው ያለው። እጣው ላይ በሚደርሳቸው ቅደም ተከተል መሰረት ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ በቅደም ተከተል እንደሚቀመጡ በመጠቆም።
 
በለይኩን ዓለም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.