Fana: At a Speed of Life!

የተሻለ ጥራት ያለው አገልግሎት ለሰጡ 10 የፌዴራል መንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ከኢፌድሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመሆን የመንግስት አገልግሎት ጥራት ላይ ያዘጋጀው ልዩ ውድድር ማጠቃለያ ፕሮግራም ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ 10 የፌዴራል መንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደታቸው ተመዝኖ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ከአስሩ መካከል የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በተሻለ መልኩ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት በመቻሉ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ቲቪ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ደግሞ የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገቢያ ባለስጣን፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን የማዕረግ ተሸላሚ ሆኗል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ደግሞ የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ሲወስድ እንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ተቋም የአፈፃፀም ውጤቱ ዝቅተኛ ነው ተብሏል።

የዚሁ ፕሮግራም ላይ ታዳሚ የነበሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በጥራት ሲታጀብ ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ወሳኝ ነው።

የጃፓንን የእድገት መንገድ ያነሱት አፈ ጉባኤው ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት፣ እውቀትን መሰረት ያደረገ የሲቪል ሰርቪስ ግንባታና የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ከራሷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማጣጣሟ ውጤታማ አድርጓታል ብለዋል።

ኢትዮጵያም በዋናነት አስፈላጊው እውቀት የጨበጠ ብቃት ያለው ሲቪል ሰርቪስ መገንባት ይገባታል ማለታቸውን ኢዜአ በዘገባው ላይ አስፍሯል።

ይህ ሲሆን የአገሪቷን የእድገት ውጥኖች በተሻለ ጥራትና ወጪ መከወን ያስችላል ነው ያሉት።

በዘርፉ እስካሁን የሚያጋጥመውን የእቅድ ትግበራ ችግር ለመፍታትም በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ስብሳቢና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልድሃናም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ።

ሁለት ተቋማት በጋራ ሆነው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሰረት ሲመዘን ምን እንደሚመስል ማመላከት ያስፈለገውም ለዚሁ ነው ይላሉ።

የተጀመረው አገራዊ ለውጥም ፈር መያዝ የሚችለው የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በሚገባ መደገፍ የሚችል የመንግስት አገልገሎት ሰጪ ዘርፍ ሲኖር መሆኑንም አስታውሰዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ እንዳሉትም በቀጣይ ዘርፉን ማዘመን የሚያስችሉ አሰራሮች ይተገበራሉ።

ብቃት ያለው አምራች ዜጋ በስፋት ወደ ዘርፉ እንዲገባና የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አሰፈጻሚ አቶ ቴድሮስ መብራቱ፤ የአስሩ አገልግሎት ስጪ ተቋማት ምዘና የአገልግሎት ጥራትን ማዕከል ባደረገ መንገድ ነው ብለዋል።

አሰራሩ አገልግሎቱን በጥራት መከወንና እቅድን ማሳካት ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ወጪ ቀንሷል የሚለውንም ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።

ለአብነትም የገቢዎች ሚኒስቴርን ጠቅሰው በዓመት ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ምን ያህል ወጪ አወጣ የሚለውም ይገመገማል ብለዋል።

ከ12 ዓመታት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት እስካሁን የአምራች ኢንዳስትሪ ዘርፉን ሲያወዳድር የቆየ ሲሆን አሁን በልዩ ሁኔታ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን መዝኗል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.