Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር እና በምርጫ ቦርድ መካከል ሲታይ የነበረው የፍርድ ቤት ክርክር ውሳኔ ተሰጠው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር ፓርቲ እና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መካከል ሲታይ የነበረው የፍርድ ቤት ክርክር ውሳኔ ተሰጠው።
ውሳኔውን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት 2ኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ሲሆን÷ ፓርቲው እራሱን እንዲከላከል በምርጫ ቦርድ በኩል እድል መስጠት አለበት ሲል ነው የወሰነው።
የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር ፓርቲ በየካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ ያለአግባብ ተሰርዣለሁ በማጣራት ሂደቱም እኔን አላሳተፈም፤ ይህ ደግሞ በህገመንግስቱ የተጠቀሰውን የመንግስት አሰራር ተጠያቂነት መርህን የተከተለ አይደለም ሲል መከራከሪያ ነጥብ አንስቷል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ከፓርቲው 120 አባላት ናሙና 29 ብቻ ነዋሪነታቸው የተረጋገጠ እና 91ዱ በጠቀሰው አድራሻቸው ነዋሪ አለመሆናቸውን በማጣራቴ ለመሰረዝ ተገድጃለሁ ብሎ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ቦርዱ አደረኩት ባለው ማጣራት አብዛኛው በስልክ ከመሆኑም በላይ ግልጽነት የጎደለው አሳታፊ ያልሆነ እና የሃገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነውም ብሏል።
ማድረጉን ከመጥቀስ ውጪ ናሙና እንዴት እንደመረጠ፣ የናሙና ማረጋጋጫ ቦታዎችን በምን መመዘኛ እንደመረጠ ምን አይነት የመረጃ ማጣሪያ መንገድ እንደተጠቀመ በተጨማሪም እነዚህ ተግባራት ሲከናወኑ ባለድርሻ አካላትን የማሳወቅ፣ አሰራሩን ግልጽ የማድረግ እና የማሳተፍ ግዴታውን ባለመወጣቱ፤ ፓርቲው ተደራጅተን የመታገል ፖለቲካዊ መብታችንን ከማሳጣቱም በላይ ሂደቱ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 12 የተደነገገውን የግልጸኝነት መርህ እና ግምትን ያላገናዘበ ነው ሲል መከራከሪያ ነጥብ አንስቶ ነበር።
ቦርዱም ውሳኔ ላይ ለመድረስ የቀበሌ፣ የከተማና የወረዳ መስተዳድሮች አቅርበዋል ያለውን መረጃ ብቻ መሰረት አድርጎ ነው በማለትም ተከራክሯል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በሃገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኛው በገጠሩ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ መታወቂያ አውጥቶ የመጠቀም ባህል የሌለው በመሆኑ የቦርዱ ማስረጃ የተሟላ አይደለም ሲልም ፓርቲው ተከራክሮ ነበር።
ክርክሩን የመረመረው ፍርድቤቱ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ምዝገባ ሂደት የመሰረዝ ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት ፓርቲው እራሱን እንዲከላከል እድል የተሰጠው መሆኑን አያሳይም ብሏል፡፡
በዚህ ምክንያት ፓርቲውም በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ከምዝገባ ከመሰረዙ በፊት ፓርቲውን በአዋጅ ቁጥር 98(3) ላይ የተጠቀሰውን እራሱን የመከላከል መብትን አለመጠበቁ አግባብ አይደለም ሲል ፍርድቤቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1163/2011 አንቀጽ 98 (4) መሰረት ውሳኔውን ሰጥቷል።
በውሳኔው መሰረት ቦርዱ ታህሳስ 9 ቀን 2013 ዓ.ም ፓርቲው ከምዝገባ ሂደት እንዲወጣ ሲል የሰጠው ውሳኔ መሻሩን አስታውቋል።
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ከምርጫ ሂደት ለመሰረዝ ምክንያት ባደረገው ጉዳይ ላይ ፓርቲው መካላከያ እንዲያቀርብ ካደረገ በኋላ ከምዝገባ ሂደቱ ሊወጣ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን በተመለከተ ግን እራሱ ምርጫ ቦርዱ የመሰለውን ይወስን ሲል ፍርድቤቱ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.