Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚተኛበት 4 ሺህ 854 ሄክታር ደን ሁለተኛው ዙር ምንጣሮ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)  ታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴው ግድብ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ሁለተኛ ዙር  የደን ምንጣሮ ሊካሄድ መሆኑን  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቴክኒክ እና ሙያ ስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም ፤ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴውን ግድብ ውሃ ሙሌት ለማከናወን ውሃ የሚተኛበት ቦታ 4 ሺህ 854 ሄክታር ደን ይሸፍናል ብለዋል።

የውሃው መጠንም ከመጀመሪያው ዙር በአራት እጥፍ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የደን ምንጣሮውን ለማከናወን በተገባደደው ሳምንት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር  ስምምነት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ወጪው ከ81 ሚሊየን  ብር በላይ እንደሚሆን  አስረድተዋል፡፡

ምንጣሮውን ለማከናወን ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ከአምስት ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶች ካቀፉ 500 ኢንተርፕራይዞች ጋር ኤጀንሲው ውል እየገባ መሆኑንና ይህም በሳምንት እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል፡፡

ለስራው  ወጪ ከሚሆነው ገንዘብ ውስጥ 20 በመቶ  ቅድመ ክፍያ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚለቀቅ የሚጠበቅ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የደን ምንጣሮ ስራውን በአንድ ወር ጊዜ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አቶ በሽር ገልጸዋል፡፡

ውሃው በሚተኛበት ከግድቡ ግራ እና ቀኝ የሚገኙ ሸርቆሌ፣ ጉባ፣ ወምበራ እና ሰዳል ወረዳዎች የምንጣሮውን ስራ 40 በመቶ እንዲያከናውኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ቀሪው 60 በመቶ የምንጣሮ ስራ ደግሞ ለሌሎች የክልሉ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች መከፋሉን አብራርተዋል፡፡

እያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ ዝቅተኛ 10 ሄክታር ከፍተኛው ደግሞ 20 ሄክታር ደን ተረክበው ምንጣሮ እንደሚያከናውኑ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

 

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.