Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲስ ወግ የውይይት መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተካሄደ ፡፡
ውይይቱ “ሰላምና ደኅንነት በምርጫ ወቅት” በተሰኘ ወቅታዊ ጭብጥ በሶስት ክፍለጊዜዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው የተካሄደው።
የመጀመሪያው ክፍል በሰላማዊ ምርጫ መገለጫዎች እና መስፈርቶች ላይ ሲያተኩር ሁለተኛው በምርጫ ወቅት ሰላምን ለማስፈን ሰላምን የሚያንጹ ሀገር በቀልና ዘመናዊ ተቋማት ሚና ተዳሷል፡
ሶስተኛው ክፍል ደግሞ ሐሰተኛ መረጃ በሰላማዊ ምርጫ ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ መግታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
በውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዶክተር መሰንበት አሰፋ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ሰብዓዊ መብትን እና የህግ የበላይነትን ማክበር ከሁሉ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ምርጫው ዴሞክራሲ እና ነጻነት የሚረጋገጥበት ቢሆንም ሁለቱም ለሚፈልጉት ስርዓት ሁሉም አካል ራሱን ማስገዛት አለበትም ነው ያሉት።
በምርጫ ሂደት ማሸነፍም መሸነፍም እንደመኖሩ የበዛ ፖለቲካዊ ጉጉት ከእውነታ ጋር ሊታረቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች እውነታውን ተገንዝበው ወደ ተሻለ የፖለቲካ ስርዓት ለመሸጋገር መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል ።
ሌላኛዋ የመነሻ ጽሑፍ አቅራቢ ህይወት አለማየሁ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ አስቀድመው የተካሄዱ ምርጫዎች በቀጣዩ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ማለፋቸውን አውስተዋል።
በዚህ ምክንያት ቀጣዩ ምርጫ ያለፉት ምርጫዎች ባለ ዕዳ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህን ችግር ለማስተካከል ብሎም ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና የተሳካ እንዲሆን ሁሉም አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አንስተዋል።
አያይዘውም ህዝቡ መብቱ እንዲከበርለት የሚፈልገውን ያህል ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባና የፖለቲካ ፓርቲዎችም ስለ ሰላም ለራሳቸው ደጋፊዎች ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባቸውም አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም በተቋማት መካከል የተሟላ ቅንጅት መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍ፡፡
በዓላዛር ታደለ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.