Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን በመስጠት ተጠናቋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ጁል ናንጋል እንዳሉት በክልሉ ያለውን ሰላም ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ለማረጋገጥ አመራሩ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል፡፡
መጪው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በኃላፊነት መንፈስ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
የዴሞክራሲ ምህዳሩን ከማስፋት አንፃር መንግስት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር በሰላም፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙሪያ የጀመራቸውን በመርህ ላይ የተመሰረተ መልካም ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል የምክር ቤት አባላትና በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት ህዝቡን በማስተባበር ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ጉባኤው በሶስት ቀናት ቆይታው ያለፈውን ግማሽ በጀት ዓመት የክልሉን የልማትና መልካም አስተዳደር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች የዕቅድ ክንውን ሪፖርት አዳምጦ አጽድቋል፡፡
በተጨማሪም የቀጣይ ግማሽ በጀት ዓመት የተከለሰ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ፣ የአምስት ረቅቅ አዋጆችና የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠት ተጠናቋል፡፡
በዚህም መሰረት አቶ ቲቾት ኩመዳንን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ቡን ዊውን የውሃና መስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊ ፣አቶ ቸንኮት ቾትን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊና የ6 ቋሚ ኮሚቴ ሹመት ማፅደቁን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬተሪ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.