Fana: At a Speed of Life!

ሐሰተኛ መረጃ  በሰላማዊ ምርጫ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ሐሰተኛ መረጃ በሰላማዊ ምርጫ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ መግታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ አተኩሮ በአዲስ ወግ ውይይት ተካሄደ።

ውይይቱ ሰላም እና ደህንነት በምርጫ ወቅት በተሰኘ ርዕስ ስር ነው የተካሄደው፡፡

በውይይቱ እስክንድር ፍሬው በቮይስ ኦፍ አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት አስተባባሪ በአወያይነት፣ ኤደን ብርሀኔ በዓለም አቀፍ ተቋም የመረጃ ማጣሪያ ባለሙያ እና ሰለሞን ጎሹ የመገናኛ ብዙኀን ተኮር የሕግ ባለሙያ በተወያይነት ተሳትፈዋል፡፡

ከተወያዮቹ መካከል አቶ ሰለሞን ጎሹ በውይይቱ ላይ የሀሰት መረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሕግ ማዕቀፍ ባላቸው ሀገራት በህግ እንደሚዳኝ አስረድተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀሰተኛ መረጃ በአጠቃላይ በዴሞክራሲ ግንባታ እንዲሁም በምርጫ ሂደት ዕንቅፋት ሲሆን ይታያልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ሳይነካ የተከለከሉ አጥፊ ተግባራትን ከነቅጣታቸው እና መረጃውን ከስርጭት ከማውጣት ሂደቱ እንደሚዘረዝርም ነው ያብራሩት።

ከማኅበራዊ ሚዲያ መገልገያዎቹ ባለቤቶች ጋር ክንውንን የመከታተልን ተግባርም ይጠይቃል ብለዋል።

በተጨማሪም ወደ ሕግ ከመገባቱ አስቀድሞ ማስተማርና ቀድሞ መከላከል የተመረጠው አካሄድ መሆኑንም የህግ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ጎሹ ማንሳታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኤደን ብርሀኔ በበኩላቸው የሀሰት መረጃ ውስብስብ ገጽታ ያለው ሲሆን፣ መፍትሔው ማስረጃ መፈለግና ከምንጩ ትክክለኛውን መረጃ ማጣራት ነው። የሚሰራጨው መረጃውን በሚያጋሩ አካላት ሁሉ ስለሆነ መደበኛውም፣ ማኅበራዊውም መገናኛ ብዙሀን መረጃን ማጣራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ መረጃን የምናገኝበት ትክክለኛው ምንጭ የቱ እንደ ሆነም ማወቅ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

እንዲሁም የሚሰራጩ መረጃዎች ውሳኔን እና አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ውጤትን ስለሚያስከትሉ የሚያጋጥሙ መረጃዎችን መዝኖ የማይጸጽት ውሳኔ መውሰድ ያስፈልገናል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ብሔራዊ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የሀገር አቀፍ ምርጫ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የ2013 ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ተአማኒ መሆን እንዲችል ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ሁኔታ መመቻቸቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሕዝቡ በነጻነት የፈለገውን እንዲመርጥ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አስፈጻሚ አካላት እንዲሁም እንደ መገናኛ ብዙሀን ያሉ አጋዥ አካላት ድርሻቸውን በነጻነት እንዲከውኑ መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግበትን መንገድ አመቻችቷልም ነው ያሉት።

ሂደቱ በአጠቃላይ የሚዳኘው በሕግ እና በሕግ አግባብ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህ መሠረት ከልዩ ልዩ የመንግሥት አካላት የተውጣጣ ሀገር አቀፍ የምርጫ ኮሚቴ መቋቋሙንም አስታውቀዋል።

ኮሚቴው ዕለታዊ የመረጃ ልውውጥ በማካሄድ ዕቅድ አዘጋጅቶ በፌደራልና በክልል አስተዳደሮች ዘንድ ያሰራጨ ሲሆን፣ እስከ ዞን ድረስ ለጸጥታ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሰርቶ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጿል።

እጩዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ታዛቢዎች፣ የምርጫ አስፈጻሚ አካላት፣ የምርጫ ቁሳቁስ፣ የምርጫ ጣቢያዎች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸውና ሂደቱ ያለ እንቅፋት እንዲከናወን የጸጥታ አካላት በየስፍራው ድጋፍ ያደርጋሉም ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.