Fana: At a Speed of Life!

ፖሊስ በእነ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድህን ፍቃዴ መዝገብ ያልቀረቡ ተከሳሾችን እንዲያቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሬዲዮ ግንኙነትን በማቋረጥ በእዙ ላይ ጥቃት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው በተከሰሱት መኮንኖች መዝገብ ያልቀረቡ ተከሳሾችን ፖሊስ እንዲያቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠው።

ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠባቸው እነ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድህን ፍቃዴ እና ሌሎች ተከሳሾች ናቸው፡፡

ተለዋጭ ቀጠሮውን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጸረ ሽብርና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡

በባለፈው ቀጠሮ ዐቃቤ ህግ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የመከላከያ ሰራዊት የሬዲዮ ግንኙነትንና በአካባቢው መብራት በማቋረጥ በሰሜን እዝ ጦር ላይ ጥቃት እንዲደርስ በማድረግ፥ በወቅቱ የቴክኒክ ባለሙያዎችን እንዲሁም ተረኛ የጥበቃ አባላትን በማገትና በማስወገድ ለጥቃቱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እና የሰራዊቱን ሬዲዮና የተለያዩ መሳሪያዎችን ለህወሓት የጸረሰላም ቡድን አሳልፈው በመስጠትና የመከላከያ ግንኙነትን በማስጠለፍ እንደተሳትፏቸው በየደረጃው ክስ እንደቀረበባቸው ይታወሳል፡፡

ይሁንና ክስ ከተመሰረተባቸው 21 ተከሳሾች መካከል 14ቱ በችሎት ያልቀረቡ ሲሆን፥ ፖሊስም ያልቀረቡ ተከሳሾችን ይዞ እንዲያቀርብ ታዞ ነበር፡፡

ፖሊስ በዛሬው ቀጠሮ ተከሳሾቹን አለማግኘቱን ገልጾ በቀጣይ ከመከላከያ ጋር በመነጋገር ተከሳሾቹን አፈላልጎ ለማቅረብ አንድ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድቤቱም ተከሳሾቹን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ለሚያዚያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.