Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ ለማስጀመር እየተሰራ ነው – ዶ/ር ሙሉ ነጋ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በክልሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ ለማስጀመር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታወቁ፡፡

ዶክተር ሙሉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ያለፉትን 100 ቀናት ምን ይመስሉ እንደነበር እየተገመገመ ይገኛል ብለዋል፡፡

በ100 ቀናት ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች ተለይተው መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የመቐለ ከተማ ከንቲባን ከኃላፊነት ማንሳት ጀምሮ የግምገማ ውጤቱን መሰረት ያደረገ ምደባ እና የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዕርዳታ አቅርቦቱ ለ4 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች መድረሱን የገለጹት ዶክተር ሙሉ መቐለን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች በስርጭት ፍትሃዊነት አኳያ የሚታዩ ክፍተቶች እንዳሉ መገምገማቸውንም ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ዙር የዕርዳታ ሂደት መጠናቀቁን የጠቀሱት ዶክተር ሙሉ ሁለተኛ ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ ለመጀመር ትክክለኛ መረጃ እየተያዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተፈናቃዮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ1 ሚሊየን በላይ መድረሱን ጠቅሰው፥ በመቐለና በሽረ አካባቢ መጠለያ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት፡፡

በተጨማሪም የተበተነ ኃይል መኖሩን ያነሱት ዶክተር ሙሉ ከእነሱ በተጨማሪ ታጣቂ ያልሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሸሸጉት ኃይሎች ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይመለስ ሐሰተኛ ዜናዎችን እንደሚያሰራጩም ነው ያነሱት፡፡

በአራት ወራት ውስጥ መንግስት ደመወዝ መክፈሉን ጠቅሰው የመንግስት አገልግሎት ግን በሚገባው መልኩ አለመጀመሩን ነው የጠቀሱት፡፡

ዶክተር ሙሉ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ችግር ለሚፈጥሩ አካላት ትዕግስት አይኖርም ብለዋል፡፡

ህይወት መቀጠል አለበት ያሉት ዶክተር ሙሉ አገልግሎት ካልተጀመረ የሚከፈል ደመወዝ አይኖርም፤ በቅርቡም የማስተካከያ እርምጃዎች ይወሰዳሉም ነው ያሉት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.