Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር አለምፀሀይ መሰረት ከዩጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዩጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለምፀሃይ መሰረት ከዩጋንዳ የመከላከያ ሚኒስትር  አዶልፍ ካሳይጃ ጋር በሁለትዮሽ እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በወቅቱም የሀገራቱ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱ በመከላከያ ዘርፍም በአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ሃይል (AMISOM) በኩል ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም በዘርፉ ያሉት ስምምነቶች አፈጻጸም ላይ ውይይት ተደርጓል።

በዚሁ ወቅት አምባሳደር አለምፀሃይ መሰረት የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ለሚኒስትር አዶልፍ ካሳይጃ  አስረድተዋል።

በዚህም  የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀም የመከላከያን ሰንሰለት ለመስበር የሞከረውን  ጥቃት ለመከላከል መንግስት የወሰደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰአት መንግስት በጽንፈኛ ቡድኑ የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን መልሶ መገንባትና በክልሉ የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እያደረገ ከመሆኑም ባለፈ ክልሉን ለሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎችና የሚዲያ ተቋማት ያለገደብ ክፍት ማድረጉን  አስረድተዋል፡፡

በሌላ መልኩ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ትኩረቱን ወደ ትግራይ ክልል ባደረገበት ወቅት ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት በሀይል መያዟን አስረድተዋል።

ይህም ድርጊት በሀገራቱ መካከል ያለውን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ  ስምምነቶች የጣሰ እንደሆነ ገልፀው ÷ አሁንም ኢትዮጵያ ወንድም ከሆነው የሱዳን ህዝብ ጋር ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሆነች ገልፃዋል።

ሚኒስትሩ አዶልፍ ከሳይጃ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በአድዋ ድል ባስመዘገበችው ደማቅ ድል መላው አፍሪካ የቀኝ ግዛትን ቀምበር ለመስበር  ተምሳሌት አድርጓት ነጻነት እንደተቀዳጀ እና ሉዓላዊነቷን በማስከበር ከአፍሪካውያን ፈር-ቀዳጅ የሆነች ታላቅ ሀገር እንደሆነች ሁሌም መዘንጋት እንደሌለበት አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ወቅታዊ ችግሮችን የማለፍ አቅም እንዳለው ለዚህም ጽኑ እምነት እንዳላችው ገልጸዋል።

ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጋር ያለው ችግር በአፍሪካዊ ወንድማማችነት እና ስምምነቶችን እንዲሁም የተቀመጡ መፍትሄዎችን በማክበር በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት በጎ አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባ በዚህም ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰደችውን እርምጃ አድንቀዋል።

በመጨረሻም ሁለቱ ሀገራት በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እና ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር መግባባት  ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.