Fana: At a Speed of Life!

በወላይታ ሶዶ ከ8 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የማስፋፊያ ስራ ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት በከተማዋ ባሉ አዳዲስ መንደሮች 8 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግንባታ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከተከናወነባቸው መንደሮች መካከል በአምስቱ ከ400 በላይ ደንበኞች ሀይል ማግኘት የጀመሩ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ከተቋሙ ጋር ውል እየፈፀሙ መሆኑን የወላይታ ዲስትሪክት የደንበኞች አገልግሎት፣ ሽያጭና ግሪቫንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አንዷለም አብርሀም አብራርተዋል፡፡

በዲስትሪክቱ አልፎ አልፎ የሽቦና የፊውዝ ስርቆት ስለሚፈጸም ህብረተሰቡ መሰረተ ልማቱ የራሱ መሆኑን በመገንዘብ ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የዲስትሪክቱ የስርጭት ፣ ኮንስትራክሽንና ኦፕሬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ገረሱ ቴጋ በበኩላቸው በከተማው ስምንት መንደሮች የተከናወነው የማስፋፊያ ግንባታ ወጪ የተሸፈነው የከተማው አስተዳደር በመደበው 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በጀት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም አንድ ባለ 100 ኪ.ቮ እና ስምንት ባለ 315 ኪ.ቮ ትራንስፎርመሮች፣ ከ420 በላይ የዝቅተኛ እንዲሁም አራት ኪ.ሜ የሚሸፍን የመካከለኛ ሀይል ማከፋፈያ መስመር ምሰሶዎች መተከላቸውን መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አስተዳደሩ በከፈለው ተጨማሪ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር 26 የዝቅተኛና 43 የመካከለኛ ሀይል ማከፋፈያ መስመር ምሰሶዎች መተከላቸውን የገለፁት ሀላፊው የመስመር ዝርጋታና የትራንስፎርመር ተከላ በአካባቢው ባለው የወሰን ማስከበር ችግር ያልተከናወነ ሲሆን ችግሩ ሲፈታ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.