Fana: At a Speed of Life!

ለግድቡ ስኬትና ለሀገር ሉዓላዊነት ተባብረን የምንቀሳቀስበት ወቅት ላይ እንገኛለን – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ10ኛ ዓመትን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ የልማት እና ዕድገት ውጥኗን በፍጥነት ለማስቀጠል ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም መሰረት ከሚጥሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተው ለኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከምንም በላይ በቀዳሚነት የሚጠቀስበት ትልቁ ምክንያት ታሪካዊ ትርጉም እና ኢኮኖሚያዊ ፍቺ በመያዙ መሆኑንም ገልፀዋል።

“ለዘመናት ያለአንዳች ፋይዳ ሲፈስ የነበረው ታላቁን የአባይ ወንዝ ለሃይል ማመንጫነት ሙሉ በሙሉ በራስ ሃሳብ፣ ጉልበት እና ገንዘብ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት የመሰረተ ድንጋይ በማስቀመጥ አሁን የግንባታውን ሂደት ወደ ማገባደጃ ምዕራፍ መሸጋገራችን ታሪካዊ ትርጉሙን ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል” ብለዋል።

በተያያዥነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽለው ከመሆኑ ባሻገር፤ ለታችኛው ተፋሰስ እና ለቀጠናው ሃገራት በሃይል ልማት ጠንካራ ትስስር መፍጠር ማስቻሉ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፍቺ ይይዛልም ነው ያሉት።

ባለፉት የፕሮጀክቱ የግንባታ ዓመታት በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ዙሪያ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት እና የዕርምት ዕርምጃዎችን በትኩረት በመውሰድ ግንባታው ወደ ማገባደጃ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተችሏልም ብለዋል።

ለዚህም ከመነሻ ጀምሮ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ሃሳባቸውን እና ድምፃቸውን በመስጠት ፕሮጀክቱ ወደ ማገባደጃው ምዕራፍ እንዲሸጋገር ድጋፍ ላደረጉ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ለሚኖሩ ወገኖች በብሄራዊ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤቱ እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል፡፡

በዚህ ዓመታት በጠንካራ የሃገር ፍቅር ስሜት የታየው ህዝባዊ ተሳትፎ እና ንቅናቄ ለቀሪ የፕሮጀክቱ ስራ ስኬታማ አፈፃፀም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.