Fana: At a Speed of Life!

ከህወሓት ጋር በመቀናጀት ተልዕኮ ፈጽመዋል የተባሉ ስድስት የትግራይ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻዎች ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 24 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተልዕኮዎችን በመፈጸም ላይ እንዳሉ ተይዘዋል የተባሉ ስድስት ተጠርጣሪ የትግራይ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻዎች ቂሊንጦ ማረሚያቤት እንዲወርዱ በፍርድ ቤት ታዘዘ።

ወደ ቂሊንጦ ማረሚያቤት እንዲወርዱ የታዘዙት ሻምበል ጻዲቅ ኪሮስ፣ ዋና ሳጅን ብርሃኑ ፍጹም፣ ዋና ሳጅን አሰፋ መአዛ፣ ዋና ሳጅን ሞገስ ደሳለኝ፣ ሃይሌ አብርሃ እና ፈይሳ ተካ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ ከህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተልዕኮዎችን በመፈጸም ላይ እንዳሉ ተይዘዋል ተብለው ምርመራ ሲከናወንባቸው መቆየቱ ይታወሳል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ በዛሬው ችሎት በተጠረጠሩበት ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ሙከራ ወንጀል ሲያከናወንባቸው የነበረውን ምርመራ አጠናቆ  የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን አስታውቋል።

ዐቃቤ ህግም በተጠርጣሪዎቹ  ላይ የቅድም ምርመራ መዝገብ ከፍቶ ምስክር ለማሰማት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አብራርቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎቹ ላይ ለረጅም ጊዜ ምርመራ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው ለዐቃቤ ህግ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ መቃወሚያ አሰምተዋል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹን በዋስ እንዲለቀቁ የጠየቁ ሲሆን÷ በጤናቸው መታወክ ምክንያት መራመድ የማይችሉ ተጠርጣሪዎች ህክምና የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው አመላክተዋል።

ጉዳዩን የተከታተለው ችሎቱ ተጠርጣሪዎቹ  የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና እንደሚያስከለክል በመግለጽ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።

ተጠርጣሪዎቹ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በማዘዝ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ተጠርጣሪዎች ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.