Fana: At a Speed of Life!

ደመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂ ግብርናን በመደገፍ የኢትዮጵያ ጎጆዎች መብራት እንዲያገኙ ያግዛል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ደመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂ ግብርናን የሚደግፍ እና የኢትዮጵያ ጎጆዎች መብራት እንዲያገኙ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ደመና የማዝነብ ቴክኖሎጂ ማስተዋወቂያ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በርካታ ግድቦችን ለመስኖ እና ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ እየገነባች ባለችበት ወቅት ከዚህ ቴክኖሎጂ መራቅ ውጤታማ አያደርግም ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ከተፈጥሮ ጋር የሚያጋጭ ሳይሆን በተፈጥሮ የተገኘን ጸጋ በአግባቡ መጠቀም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መሰል ስራዎችን በማስፋፋት የዜጎችን ህይወት ለመቀየር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ሆኖም የሀገር ሰላም እና ወንድማማችነት ስሜት መጠበቅ ካልተቻለ ሁሉ ከንቱ ስለሆነ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በስምንት ግምባሮች የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ ጸረ አርሶ አደር የሆኑ ሀይሎችን እያጸዳ መሆኑን አስታውቀዋል ።

ደመናን ማዝነብ የአየር ሁኔታን በሰው ሰራሽ መንገድ የመቀየር ቴክኖሎጂ አካል ሲሆን፥ አላማውም ከደመና የሚገኝ የዝናብ ዓይነትና መጠንን መለወጥ ነው።

የሚከናወነውም እርጥበትን በቀላሉ የሚሰበስቡ ንጥረ ነገሮችን ወደ ደመና በመርጨትና የደመናን አካላዊ ሂደት በመቀየር ነው።

እየተከናወነ ያለው የቴክኖሎጂ ሙከራ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ጋር በተጣመረ መልኩ በአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ወራት ሲተገበር ቆይቷል።

ቴክኖሎጂው ወደ ስራ እንዲገባ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ለሙከራ የሚያገለግል የንጥረ ነገር መርጫ አውሮፕላን፣ ከመሬት ንጥረ ነገሩ የሚለቀቅበት ጀኔሬተር፣ የዝናብ ማበልጸጊያ ንጥረነገርን ጨምሮ ሌሎች እገዛዎች ተደርገዋል፡፡

በዓላዛር ታደለ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.