Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመቱ ከ22 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመቱ 22 ቢሊየን 40 ሚሊየን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ይፋ አደረገ።

በስድስት ወር አፈጻጸሙ የእቅዱን 104 በመቶ ማሳካቱንም አስታውቋል፤ ካለፈው አመት አንጻር የ32 በመቶ እድገት አሳይቷል።

ተቋሙ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶችም 73 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቱን ጠቁሟል።

የተገኘው ገቢ ከሞባይል ድምጽ 50 ነጥብ 4 በመቶ፣ ከዳታና ኢንተርኔት 27 ነጥብ 3 በመቶ፣ ከዓለም አቀፍ ንግድ ገቢ 9 ነጥብ 8 በመቶ፣ እሴት ከሚጨምሩ አገልግሎቶች 8 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች 3 በመቶ መሆኑም ተገልጿል።

የደንበኞቹ ብዛት 45 ነጥብ 6 ሚሊየን መድረሱን የጠቀሰው ሪፖርቱ፥ ይህም ከእቅዱ የ99 በመቶ አፈጻጸም ያለው እና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 ነጥብ 9 በመቶ እድገት አሳይቷል ብሏል።

በአገልግሎት አይነት ደግሞ የሞባይል ድምፅ ተጠቃሚዎች ብዛት ከ44 ሚሊየን በላይ፣ የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ 22 ነጥብ 74 ሚሊየን፣ የመደበኛ ስልክ ከ1 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ሲሆኑ፥ አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት መጠን ደግሞ 45 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱ ተነግሯል፡፡

ተቋሙ በሪፖርቱ የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ ለማሻሻልና በተለይም እያደገ የመጣውን የዳታ አገልግሎት ተጠቃሚነት ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል የኔትወርክ አቅም የማሳደግ ሥራዎች በአዲስ አበባና በክልሎች እየተከናወነ መሆኑንም ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም የደንበኞችን የቴሌኮም አጠቃቀም ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያና የአገልግሎት ጥራትን ለመጨመር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማከናወኑንም ነው የገለጸው።

እንዲሁም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች በተጨማሪ ሌሎች እሴት የሚጨምሩ 6 አዳዲስ እና 16 የተሻሻሉ የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን ለገበያ ማቅረቡንም አስታውቋል።

በዚህም ባሳለፍነው ስድስት ወራት ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች 759 ሺህ 741 ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የሶስተኛ ትውልድ (3ጂ) እና 170 ሺህ 737 የሁለተኛ ትውልድ (2ጂ) ሞባይል ኔትወርክ አቅም መፍጠር መቻሉን ጠቅሷል።

በሌላ በኩል በፍጥነት እያደገ ያለውን የዳታ አጠቃቀም ለማስተናገድ የሚያስችል የዓለም አቀፍ ጌትዌይ አቅምን በግማሽ ዓመቱ ከ71 በመቶ በላይ ማሳደግ ችያለሁም ነው ያለው።

ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የአራተኛ ትውልድ (4ጂ) ኔትዎርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው መባሉን ከኢትዮ ቴሌኮም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.