Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ኮቪድ19ኝን ለመከላከል ከወጣው መመሪያ ጋር በተያያዘ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ኮቪድ19ኝን ለመከላከል ባለፉት ሳምንታት ከወጣው መመሪያ ጋር በተያያዘ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ሙሉ ማብራሪያው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

  1. ስለ ስብሰባ፤ ስለ ስብሰባ የሚደነግገው አንቀጽ ውይይት ማድረግ የሚፈልግ የትኛውም ተቋም የተሳታፊዎቹን ቁጥር ከ50 እንዳይበልጥ የሚከለክል ሲሆን ከ50 በላይ ተሳታፊዎችን የሚያቅፉ ውይይቶች አስገዳጅ ሲሆኑ የአዳራሹን ወይም የመወያያውን ስፍራ ሰው የመያዝ አቅም አንድ አራተኛውን በመጠቀም እና ለሰላም ሚኒስቴር ወይም በተዋረድ ላሉ የክልል፣ ዞን እና ወረዳ የሰላምና ፀጥታ መዋቅሮች (በአቅራቢያ ላለ ፖሊስ ጣቢያ) በማሳወቅ ዉይይቱን ሊያከናውን ይችላል፡፡

በተጨማሪም በተሳታፊዎቹ መካከል የሚኖረው አካላዊ ርቀት ከሁለት የአዋቂ እርምጃ ሳያንስ እንዲሁም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲጠቀሙ እና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሟላ በማድረግ ማከናወን የሚቻል መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ከዚህ እና መመሪያው ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ድርጊትን የሚከለክሉ ሳይሆኑ ገደብ የሚጥሉ በመሆናቸው ገደቦቹን በማክበር የተፈለገውን ዓላማ ማሳካት የሚያስችል ህግ ነው፡፡

  1. ከምርጫ ጋር በተገናኘ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መስፋፋት ለመከላከል ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ ርምጃዎች ተፈፃሚ የሚሆነው ይህ መመሪያ ሳይሆን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የሚያወጣው መመሪያ ነዉ፡፡
  2. መመሪያው በመንግስት ተቋማት ላይም ተፈጻሚነት ያለው ስለመሆኑ፤ ለቋማችን እየቀረቡ ካሉት ጥያቄዎች መካከል አንዱ መመሪያው በመንግስት ተቋማት ቢጣስ ተጠያቂነትን ያስከትላል ወይ የሚል ነው፡፡

ከዚህ አንጻር ከመመሪያው የምንረዳው የወጣበት ዓላማ ሁሉንም የማህበረሰብ አካል በእኩል ለመግዛት ነው፡፡ ይህ ማለት በመመሪያው የተጣሉትን ገደቦችም ሆነ ግዴታዎች ጥሶ የሚገኝ ማንኛውም የመንግስት ተቋም እንደ የግል ተቋማት እና ግለሰቦች ሁሉ በህግ ከመጠየቅ የሚድንበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ነው፡፡ የመንግስት ተቋት የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች በህጉ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ምሳሌ ሆነው መቅረብ አለባቸው፡፡

ቀድመው የታቀዱ ውይይቶቻቸውን እየሰረዙ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ እያራዘሙ ወይም በበየነመረብ ለማካሄድ በመወሰን ላይ ላሉ ተቋማት ኮሚቴው ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

  1. ስለ ቅጣት፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ካለው በቀላሉ የመሰራጨት ዕድል የተነሳ ሰዎችን ማሰር አማራጭ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ወደ እስር ከመገባቱ በፊት ህዝቡን ማስተማር እና ማስጠንቀቅ የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ትምህርቱን እና መስጠንቀቂያውን ችላ ብለው በወንጀል ተግባር ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎችን በወንጀል መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

መመሪያው ያመላከተው የወንጀል ህጉም አንቀጽ 522 በድርጊቱ ጥፋተኛ የተባለ ሰው እስከ 2 ዓመት ቀላል እስራት ይቀጣል ይላል፡፡ ይህ ማለት አንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ ማስክ አለማድረግ 2 ዓመት ያስቀጣል በሚል መረዳት አደጋ አለው፡፡

ድንጋጌው ቀላል እስራቱ እስከ 2 ዓመት ቀላል እስራት ነው የሚለው፤ እስከ ከተባለ 2 ዓመት ጣራው ሆኖ መነሻ የእስራት መጠን አለው ማለት ነው፡፡ በወንጀል ህጋችን ጠቅላላ ክፍል ቀላል እስራት መነሻው 10 ቀን እንደሆነ ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም ወንጀሉ የሚያስጠይቀው በ2 ዓመት ሳይሆን ከ10 ቀን እስከ 2 ዓመት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጸመ የተባለው የህግ ጥሰት ውስጥ ያሉ የድርጊት እና የሀሳብ ክፍል ከግምት ገብቶ እንደ ወንጀሉ ክብደት ደረጃ ወጥቶለት የሚወሰን ነው ማለት ነው፡፡

በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት አንድ አጠገቡ ካለ ሰው ከ2 ሜትር በታች በሆነ ርቀት ውስጥ ተጠግቶ የቆመ ሰው እና በሽታው እንዳለበት እያወቀ ከሌሎች ጋር የተቀላቀለ፤ አብሮ የተንቀሳቀሰ ወይም ምግብ የተመገበ ሰው የወንጀል ባህሪ (አደገኝነታቸው) እኩል ሊሆን አይችልም፡፡

በመሆኑም ሰው መቀጣት ያለበት ባጠፋው ልክ በመሆኑ ቅጣት ሲጣል ይህንን ከግምት የሚያስገባ ይሆናል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.