Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ትናንት ሌሊት በደረሱ የእሳት አደጋዎች ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ወደመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 01፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ ትናንት ሌሊት በአራት የተለያዩ አካባቢዎች በደረሰ የእሳት አደጋ 7 ሚሊየን 550 ሺህ ብር ግምት ያለው ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ እንደገለጹት፤ የእሳት አደጋው የተከሰተው በአቃቂ ቃሊቲ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ በሁለት የተለያዩ አካባቢዎች ነው።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ልዩ ቦታው መልካ ሸኔ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ50 ገደማ በከብቶች በረትና በሰባት አባወራ ቤቶች ላይ ቃጠሎ ደርሶ ውድመት ያስከተለ ሲሆን፤ በአደጋው ዘጠኝ ላሞችና ሁለት ጥጆች መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ወይራ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሌሊት 7 ሰዓት ላይ በመስጂድ ቅጥር ግቢ በሚገኝ መጋዘን ላይ የእሳት አደጋ ተከስቷል።

በተጨማሪም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ልዩ ቦታው “ስኩል ኦፍ ቱሞሮው” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሌሊት 6 ሰዓት ገደማ የመኖሪያ ቤት ላይ ቃጠሎ ደርሷል።

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት “መለስ ፋውንዴሽን” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሌሊቱ 4 ሰዓት ገደማ በአንድ ማተሚያ ቤት በደረሰው የእሳት አደጋ ጉዳት ደርሷል።

እንደ አቶ ጉልላት ገለፃ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የተከሰተው አደጋ መንስኤው አባወራዎቹ የወይራ ጭስ ለማጠን በተያያዘ እሳት ሲሆን፤ በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ ስድስት የተከሰተውን አደጋ መንስኤ እየተጣራ ነው ብለዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ሁለት ወረዳዎች የደረሰው አደጋ መንስኤ ደግሞ አንደኛው በኤሌክትሪክ ምክንያት ሲሆን ሌላኛው እስካሁን ምክንያቱ አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡

በተከሰቱት አራት የእሳት አደጋዎች 7 ሚሊየን 550 ሺህ ግምት ባለው ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ቡድን መሪው፤ በተደረገው መከላከል 67 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ንብረት ማትረፍ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ከአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በተጨማሪም የአዲስ አበባና ፌደራል ፖሊስ አባላትና የአካባቢው ማህበረሰብ እሳቱን በማጥፋት ርብርብ ማድረጋቸውን በመጥቀስ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.