Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ሚኒስቴር ከክልል የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎችና ኮሚሽነሮች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰላም ሚኒስቴር ከክልል የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎችና ኮሚሽነሮች ጋር መወያየቱን አስታወቀ።

ውይይቱ በገለልተኛ ቡድን አማካሪ ማስፈፀሚያ ማንዋል እና በብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ላይ ያተኮረ መሆኑንም አስታውቋል።

የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል፥ የገለልተኛ አማካሪ ቡድን ከህብረተሰቡ መካከል በፈቃደኝነት የሚመረጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ፖሊስ የህብረተሰቡን ብዝሃነት እና ፍላጎት መሰረት ያደረገና ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል ላይ ውጤታማ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ያላቸውን እውቀትና ልምድ ለፖሊስ በማማከር የሚሰራ ነፃና ገለልተኛ የማህበረሰብ አደረጃጀት መሆኑንም ተናግረዋል።

አደረጃጀቱ ወደ ተግባር ሲገባ ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ ትክክለኛ መረጃዎችን በመሰብሰብ አቅጣጫዎችንና መፍትሄዎችን ያስቀምጣል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በህብረተሰቡና በፖሊስ መካከል መተማመንን ለመፍጠር የሚያስችልና የህብረተሰቡን ባለቤትነትና የፖሊስን ሀላፊነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም አንስተዋል።

የብሔራዊ በጎፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራምን ለማስጀመርም የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ በርካታ ስራዎች መሰራታቸው ተገልጿል።

ዋነኛ የፕሮግራሙ አካል የሆኑትና ከዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ ኮሌጆች ተመርቀው ስራ የሚፈልጉ ወጣቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ይሁን እንጅ በመረጃ እጥረት ሳቢያ በአንዳንድ ወረዳዎች በታሰበው ልክ ምዝገባ ማካሄድ ባለመቻሉ ክልሎች የታየውን የመረጃ ልውውጥ ክፍተት በመሙላት የምዝገባ ሂደቱን በፍጥነት እንዲሰሩ አቅጣጫ መሰጠቱን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.