Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት መረጃዎችን ለመለዋወጥ ሱዳን እና ግብጽ ተወካይ እንዲሰይሙ ጋበዘች

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት መረጃዎችን ለመለዋወጥ ሱዳን እና ግብጽ ተወካይ እንዲሰይሙ ጋበዙ፡፡

ለሃገራቱ የውሃ ሚኒስትሮች በጻፉት ደብዳቤ በመጭው ክረምት ከሚጀመረው የግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ መረጃዎችን መለዋወጥ እንዲያስችል ሃገራቱ ተወካይ እንዲሰይሙ ጋብዘዋል፡፡

ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ግብዣው ከሶስቱ ሃገራት በተውጣጣው ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን በተዘጋጀው የግድቡ የውሃ ሙሌት የጊዜ ሰሌዳ ስምምነትን መሰረት ያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ሂደትና የክረምት ወቅት መቃረቡን ያነሱት ሚኒስትሩ በተግራባዊና አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

የተወካዮች መሰየምም ትክክለኛ መረጃ ለመለዋወጥ ከማስቻሉም በላይ በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት በሚካሄደው ድርድር ላይ መተማመንን ለመፍጠር እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡

የግድቡ የውሃ ሙሌት የሚካሄደው ሶስቱ ሃገራት በፈረንጆቹ 2015 በደረሱት የመግባቢያ ሰነድ አንቀጽ ሀ መሰረት እንደሆነ በደብዳቤው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የግድቡ የውሃ ሙሌት በመጭዎቹ ሐምሌና ነሐሴ ወር የሚካሄድ ሲሆን፥ እንደ አስፈላጊነቱም እስከመስከረም ድረስ ሊራዘም ይችላል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.