Fana: At a Speed of Life!

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከሰባት ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ደረሰ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ቦታው ቦሌ ኢምፔሪያል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመሬት ውስጥ ተቀባሪ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የምስራቅ አዲስ አበባ ዲስትሪክት የዲስትሪቢዩሽን ኃላፊ የሆኑት ወይዘሪት ዮዲት ገብረማሪያም÷ ጉዳት የደረሰው በዋናነት የተቋሙ ንብረት በሆነ የመሬት ውስጥ ተቀባሪ መስመር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም በገንዘብ ሲተመን 6 ሚሊየን 157 ሺህ 911 ብር ይሆናል ያሉት ኃላፊዋ÷ የመልሶ ጥገና ሥራው ሲጨመር አጠቃላይ ወጪው 7 ሚሊየን 405 ሺህ 152 ብር እንደሚደርስ ገልጸዋል።

ጉዳቱ የደረሰው በአካባቢው በሚሰራው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም መሆኑንም ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

15 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የሚሆን የደንበኞችን የኃይል አቅርቦት ለማሟላት የሚያስችል መስመር መሆኑን ያነሱት ኃላፊዋ ከተጠቀሰው ጊዜም በኃላም ተደጋጋሚ ጉዳት እንደደረሰበት ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በዚህ ምክንያትም በጊዜው ከመሃል ቦሌ በስካይላይት ሆቴል አድርጎ በሚሌኒየም አዳራሽ እስከ አትላስ ባለው መስመር ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደነበር አስታውሰው÷ በተደረገው ርብርብ አገልግሎቱ እንዲመለስ መደረጉን ወይዘሪት ዮዲት አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ አቶ ገበየሁ ሊካሳ በበኩላቸው÷ ችግሩ የደረሰው ከጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን አንስተዋል።

እንደነዚህ ዓይነት ጉዳቶች ሲደርሱ በተቋሙ ሆነ በደንበኞቹ ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ በመውስድ ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓቶች በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚገዙና ብዙ ሃብት የሚፈስባቸው በመሆኑ ህብረተሰቡም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከጉዳት ሊጠብቋቸው እንደሚገባ ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል፡፡

ጉዳት ሲደርስም በቶሎ ለመተካት ያስቸግራል፣ ተጠቃሚውም ያለ ኤሌክትሪክ ለብዙ ጊዜ ያስቀራል ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራዎችን ሲያከናውን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በውይይትና በተቀናጀ መልኩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደፊትም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክሮችንና ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክረን እንሄዳለን ሲሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.