Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያይተዋል፡፡

በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሸሪፍ አብደላ ጋር በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት እና ድንበር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱም አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ሙሌት ዝግጅት ጋር በተገናኘ ከትናንት ጀምሮ ከግድቡ ስለሚለቀቀው ዉሃ እንዲሁም በቀጣይ የሚኖሩ የመረጃ ልውውጦችን ለማቀላጠፍ በሱዳን በኩል ተጠሪ እንዲሰየም ኢትዮጵያ በደብዳቤ ማሳወቋን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ምክንያት ወንድም በሆነው የሱዳን ሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገች እንደምትቀጥል ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ በሱዳን ሕዝብና መንግስት ዘንድ ስጋት ሊኖር እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የጋራ ድንበሩን በተመለከተ ባሉን ስምምነቶች እና በተቋቋሙ የጋራ ኮሚቴዎች አማካኝነት መፍትሔ መፈለግ ተገቢ የነበር ቢሆንም፤ የሱዳን ወገን በዚህ ረገድ ያለው ዝግጁነት አናሳ በመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ የተለወጠ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ስምምነቶችን መሰረት አድርጎ እልባት መስጠት እንደሚገባም አምባሳደሩ አንስተዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩም ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ወገን መረጃ መስጠቱ በጎ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስለጉዳዩ አስገዳጅ ስምምነት ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በድንበሩ ጉዳይ ተቀራርቦ መነጋገርና የሁለቱ አገራት የጋራ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ እንዲገናኙ ማመቻቸት ጠቃሚ እንደሆነ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.