Fana: At a Speed of Life!

ምርጫው በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ምሁራን እና የፖለቲካ ልሂቃን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መጪው ምርጫ በእውቀትና ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ምሁራን እና የፖለቲካ ልሂቃን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከደመራ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የአስተዳደርና መሰረተ ልማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ሰለሞን አብርሃ ምሁራን እና የፖለቲካ ልሂቃን ምርጫ ተወዳዳሪዎችን፣መራጮችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና ሌሎች የማህበረሰብ አካላትን ማንቃት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

ይህን በማድረግም ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ምሁራን እና የፖለቲካ ልሂቃን ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ እና ሌሎች ሀገራት ከምርጫ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን ችግሮች በማጤንና በመተንተን በሀገራቸው እንዳይደገም ጥረት ካላደረጉ በታሪክ ተወቃሽ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በሰጡት አስተያየት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅድሚያ መስራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ አትኩሮ በመስራት፣ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ክፍተቶችን በማረም ከምርጫው ጋር በተያያዘ የሚነሱ ስጋቶችን መቀነስ እንደሚቻል መናገራቸውን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.