Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ መርሐግብር ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ መርሐግብር በአምስት ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈረመ ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎች፣ አጋር ድርጅቶች እና ባለሀብቶች ጋር በመተባበር ለጎዳና ተዳዳሪዎችን እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎችን የዕለት ጉርስ የሚሆን ምግብ ለማቅረብ በሙከራ ደረጃ በአምስት  ክፍለከተሞች የምገባ ማዕከል ለማደራጀት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል ።

በስምምነት መርሐግብሩ ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት በከተማዋ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እነዚህን ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብም በሙከራ ደረጃ በአምስት ክፍለከተሞች ተግባራዊ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ይህን በጎ ተግባር ለመደገፍ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ላሳዩ ሆቴሎች፣ አጋር አካላት እና ባለሀብቶች በከተማ አስተዳደሩ ስም ምክትል ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

ፕሮጀክቱ ከትላልቅ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እና ሱፐርማርኬቶች የሚገኘውን ምግብ በመውሰድ በየማዕከሉ በማሰራጨት በቀን አንድ ጊዜ ለጎዳና ተዳዳሪዎች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች በማቅረብ ተጠቃሚ የሚያርግ ነው።

የምገባ ማዕከሉ በአራዳ፣ ቂርቆስ ፣ አዲስ ከተማ፣ ቦሌ እና ልደታ ክፍለከተሞች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን÷ ከተለያዩ ሆቴሎች የሚመጡ የምግብ አይነቶች  ደህንነታቸው ተረጋግጦ ለምግብነት ምቹ በሆነ ጊዜ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ ተገልጿል ።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለሚገነባው የምገባ ማዕከል ሚድሮክ ሙሉ ወጪውን የሚሸፍን ሲሆን በአራዳ ደግሞ በቻይናው የኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽን ኩባንያ አማካኝነት ግንባታ የሚካሄድ ይሆናል።

በተጨማሪም የቂርቆስ ክፍለ ከተማን የግንባታ ወጪን በኢትዮጵያ ጠለፋ መድህን አክሲዮን ማህበር በኩል የሚሸፈን ሲሆን የልደታ ክፍለከተማ በአዋሽ ባንክ አማካኝነት የሚገነባ መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሬታሪያት ጽህህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.