Fana: At a Speed of Life!

በፍርድ ቤቶች ምርጫ ነክ ክርክሮችን በልዩ ሁኔታ ለመዳኘት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከመጭው ምርጫ ጋር ተያይዞ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡ የዳኝነት ጥያቄዎች ቀልጣፋና ጥራት ያለው ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች በኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተሰጧቸውን ሃላፊነቶች በህገ መንግስቱና በስነ ስርዓት ህጉ ከተቀመጡት መሰረታዊ ድንጋጌዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለመወጣት የሚያስችላቸውን አደረጃጀትና አቅም ለመፍጠር በየበኩላቸው የቅድመ ዝግጀት ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል

በዚህ መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ከሶስቱም ፌደራል ፍርድ ቤቶች የበላይ አመራሮችና የምድብ ችሎት አስተባባሪዎች ጋር የምርጫና ሌሎች ተያያዥ ህጎችን መሰረት በማድረግ ለፍርድ ቤቶቹ ለሚቀርቡ ጉዳዮች ጥራት ያለው ፈጣን ውሳኔ መስጠት በሚቻልበት አግባብ ላይ መክረዋል።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሰፊ ውይይት ባደረጉበት በዚህ የምክክር መድረክ ከምርጫ ሂደት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ጉዳዮች በአጭር ጊዜ ውሳኔ የሚፈልጉ መሆናቸው ተመላክቷል።

ከዚህ ባለፈም ከምርጫ ሂደት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ጉዳዮችን በመደበኛው የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደማይቻል መገለጹን ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

እነዚህን ችግሮች ግምት ውስጥ በማስገባትም በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድህረ ምርጫ ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ፈጣን፣ ግልጽና ፍትሃዊ ዳኝነት ለመስጠት ፍርድ ቤቶች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራት ላይ ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ ተሰጥቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.