Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ሚዲያ ሃውስ ጋዜጠኛ ፍፁም ብርሃኔ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ሚዲያ ሃውስ ጋዜጠኛ ፍፁም ብርሃኔ እና የአይጋ ፎረም ዋና አዘጋጅና የኢትዮጵያ ተወካይ ጋዜጠኛ ታምራት የማነ በቁጥጥር ስር ውለዋል ፡፡

የ3ኛ ሻለቃ ዋና አዛዥ ሻለቃ ደረጄ ዴቢሳ እንደገለፁት፤ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር መዋቅር ውስጥ በመሆን ከፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር እየሰሩ የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ፥ የትግራይ ሚዲያ ሃውስ ጋዜጠኛ ፍፁም ብርሃኔ እና የአይጋ ፎረም ኤዲቶሪያል ዋና አዘጋጅና የኢትዮጵያ ተወካይ ጋዜጠኛ ታምራት የማነ በመቐለ ከተማ በግለሰብ ቤት ስቱዲዮ ተከራይተው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በቀጥታ ስርጭት በሚያስተላልፉበት ወቅት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በግለሰቦቹ ቤት በተደረገው ፍተሻም ለጁንታው ታጣቂ ቡድን ወደ በረሃ ለመላክ የተዘጋጁ በርካታ መድሀኒቶች፣ አልባሳትና የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ የኤሌክትሮኒክ እቃዎችና በርካታ ዶክመንቶች መያዛቸውንም ተናግረዋል።

በትግራይ በተደረገው ህግን የማስከበር ዘመቻ ጠላት የሚመካባቸውን ምሽጎች በሶሮቃ ፣ በዳንሻ ፣ በባካር ፤ በመሶበር ፤ በጨርጨርና በአይደፈር ተራሮች ላይ የተገነቡ ምሽጎችን በመስበር የጠላትን ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን በመቆጣጠር ታሪክ የማይረሳው ገድል ፈጽመዋልም ብለዋል፡፡

ሻለቃው የመቐለ ከተማ ሁለንተናዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን ለማረጋገጥ ለ24 ሰዓታት በቀንና በሌሊት የፓትሮሊንግ ስራዎችን በመስራት በከተማዋ ውስጥ በግለሰብ እጅ የሚገኙ ከቀላል እስከ ቡድን መሣሪያዎችን በማስፈታት ስርቆትና ዝርፊያ መቀነስ መቻሉንም ገልጸዋል።

በዚህም በልዩ ዘመቻዎች ሃይል 2ኛ ኮማንዶ ብርጌድ 3ኛ ኮማንዶ ሻለቃ በትግራይ ክልል ህግ በማስከበር ዘመቻ አመርቂ ግዳጅ መፈፀማቸውም ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በመቐለ ከተማ በሰፈነው ሰላም ህዝቡ የዕለት ተዕለት ተግባሩን በሰላማዊ መንገድ እየፈጸመ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም የኮማንዶ ሻለቃው አባላት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለትግራይ ክልል የሚደረገውን ሁለንተናዊ እርዳታና ድጋፎችን የተጠናከረ እጀባ በማድረግ ለህብረተሰቡ እያደረሱ ይገኛሉም ነው ያሉት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.