Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከ274 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ዘመናዊ የእግረኞች መሻገሪያ ድልድዮች ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ274 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በቀላል ባቡር መስመር እና የቀለበት መንገድ ላይ ዘመናዊ የእግረኞች መሻገሪያ ድልድዮች ሊገነቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ በቀላል ባቡር እና የቀለበት መንገድ መቋረጫዎች ለእግረኞች ምቹ ካለመሆናቸው እግረኞች መንገዱን ለማቋረጥ ረጅም ርቀት በመጓዝ ለድካም እና እንግልት እንዲሁም እራሳቸውን ለትራፊክ ግጭት አደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መንገዱን እንደሚያቋርጡ ኤጀንሲው ገልጿል፡፡

ኤጀንሲ የከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴ ሰላማዊ እና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ከሚያከናውናቸው ተግባራት መንገዶች እግረኞችን ባማከለ መልኩ ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ አንዱ ነው ብሏል፡፡

በዚህም በከተማዋ በቀለበት መንገድ እና በሁለቱ የቀላል ባቡር መስመሮች ማቋረጫዎች ላይ የሚስተዋለውን የትራክ አደጋ እና መጨናናቅ ችግር ለመፍታት  አራት ቦታዎች ተመርጠው የእግረኛ ድልድይ በመገንባት እግረኛውን እና ተሽከርካሪን በመለየት ችግሩን ለመፍታት ዘመናዊ የመንገድ ማቋረጫ ድልድዮች ግንባታን ለማከናወን ኤጀንሲው የቅድመ ዝግጅት ስራን አጠናቆ የኮንትራት ስምምነት እንደተፈራረመ አስታውቋል።

ኤጀንሲው የድልድዮቹን የዲዛይን ስራን ጨምሮ ግንባታውን ለማከናወን ባወጣው ግልፅ አለም አቀፍ ጫረታ የቻይናው ዥ ያንግ ዚ የተባለ የግንባታ ኩባንያ በ274 ሚሊየን 965 ሺህ ብር አጠቃላይ ወጪ በከተማዋ በተመረጡ አራት ቦታዎች ጉርድ ሾላ፣ መሪ ሲ ኤም ሲ፣ ጎጃም በረንዳ እና በአዲሱ ሰፈር ሃኪም ማሞ በተባሉ አከባቢዎች ግንባታውን ለማከናወን የኮንትራት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

አራቱ የተመረጡ አካባቢዎች እግረኞች በብዛት የምንቀሳቀሱባቸው የቀላል ባቡር መስመሮች እና የቀለበት መንገዶች ሲሆኑ እግረኞች መንገዱን ለማቋረጥ በጣም ሲቸገሩባቸው የነበረ በተለይ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአቅመ ደካሞች መንገዱን መቋረጥ እጅግ ፈታኝ የነበሩ አካባቢዎች ናቸው፡፡

ከፍተኛ የእግረኞች መተላለፊያ አከባቢዎች ላይ የእግረኞች ማቋረጫ ድልድዮችን መገንባት ያስፈለገበት ዋና ዓላማ በአካባቢዎቹ በቀላል የከተማ ባቡር እና ከፍተኛ የተሽከርካሪዎች ምልልስ ያለባቸው በመሆኑ እግረኞች በብዛት የሚንቀሳቀሱበት በመሆኑ በህገ-ወጥ መልኩ መንገዱን ሲያቋርጡ ለትራፊክ ግጭት አደጋዎች መጋለጥ የነበራቸውን ስጋት በመቀነስ ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ፣ መንገዶቹን ለማቋረጥ የነበረውን የእግረኞች ድካም እና እንግልት ለመቀነስ እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን እና አቅመ ደካሞችን ባመከለ መልኩ ምቹ፤ ቀላል እና ዘመናዊ የእግረኛ መሻገሪያ መንገድን ለመፍጠር ነው፡፡

በከተማዋ በተጠቀሱት አራት ቦታዎች የሚገነቡት ድልድዮች ዘመናዊ እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ አካተው የያዙ መሆናቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከእግረኞች መሻገሪያነት በተጨማሪ ለተለያዩ ግብይት የሚሆኑ ሱቅ፣ የባስ እና የባቡር ትኬት መቁረጫ ቢሮዎች፣ ዘመናዊ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችም ይኖሩታል፡፡

የሚገነቡት ድልድዮች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ለከተማችን ውበት የሚያጎናፅፉ ሲሆን ከዚህ ቀደም በከተማችን ከተሰሩት ድልድዮች በዓይነትም ሆነ በአሰራር የተሻለ እና ዘመናዊ የሆነ ብሎም ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።

የሚገነቡት የእያንዳንዱ ድልድዮች ርዝመት 40 ሜትር ሲሆን ወደ ላይ ከፍታው 5 ነጥብ 4 ሜትር ሆኖ ስፋቱ እንደየ መሻገሪያው አካባቢ እና የእግረኞ ብዛት የሚወሰን ሆኖ ዝቅተኛው 4 ሜትር ይሆናል፡፡

ጨረታውን አሸንፎ ከኤጀንሲው ጋር የኮንትራት ውል የፈረመው ዥ ያንግ ዚ የግንባታ ኩባንያ የእግረኞች መሸጋገሪያ ድልድዮቹን ግንባታ በ300 ቀናት እንደሚያጠናቅቅ በስምምነቱ ተጠቅሷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.